በተያዘው በጀት ዓመት የገበያ ማረጋጋት ልዩ ትኩረት ይደረግበታል

89

መስከረም 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት በገበያ ማረጋጋት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን እና በ2014 የያዘውን ዕቅድ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሺመቤት ነጋሽ፤ ድርጅቱ ከዚህ በፊት ከነበሩበት የተለያዩ ችግሮች ተላቆ የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ገበያን ለማረጋገት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያ ማረጋጋትና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ዋነኛው ትኩረቱ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አንስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በጨርቃጨርቅ እና አልባሳት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ኮንስትርክሽንና ኬሚካል ዘርፎች አቅርቦት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የድርጅቱን ተልኮ በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል እና ባለድርሻ አካላትን በሚገባ ለማገልገል ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ "ከግዥም ሆነ ከአቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እንሰራለን" ብለዋል።

የግብይት ስርአቱን ዲጂታል በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ብልሹ አሰራርን ለመቆጣጠር እንደሚጥር ጠቁመዋል።

በ2013 በጀት ዓመት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ተመድቦ ለተለያዩ የምግብና መሠረታዊ ፍጆታዎች ግዥ መዋሉን ጠቅሰዋል።

"በ219 ሚሊየን ብር ሲሚንቶ፣ ከ23 ሚሊየን ሊትር በላይ ፓልም ዘይት እና 6 ሚሊየን ሊትር ፈሳሽ ዘይት እንዲሁም ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስኳር በቅናሽ ዋጋ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ተደርጓል" ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ድርጅቱ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱንም ተናግረዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ተካ ገብረየስ ድርጅቱ ያለበትን ውስብስብ ችግሮች በመፍታት ገበያን ለማረጋጋት እና የኢንዱስሪ ምርቶችን ለማቅረብ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳፉ ባለደርሻ አካለት በበኩላቸው በድርጀቱ ያለው መሻሻል የሚበረታታ መሆኑን ተናግረው፤ በቀጣይ የግብዓት አቅርቦትም ሆነ የገበያ ማረጋጋት ላይ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም