ለአገራችን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ክብር በጋራ ልንቆም ይገባል"

49

መስከረም 14 / 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወቅት ለአገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ክብር በጋራ መቆማችንን ማረጋገጥ አለብን ሲሉ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት" ንቅናቄን ተቀላቅለዋል። 

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን የምናሳይበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ክብር በጋራ መቆማችንን ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት" ሃሳብ አፍላቂ ወጣቶችም ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲቆሙ በማድረጋቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። 

የዘመቻው ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የውጭ ተጽእኖ መመከት በመሆኑ ለሀገር መጽናት የኢትዮጵያዊያን በጋራ መቆም የሚሻ ሁሉ የዚህ ዘመቻ አካል መሆን አለበትም ነው ያሉት። 

አስተያየታችውን ለኢዜአ የሰጡ የተቋሙ ሰራተኞች ዘመቻው የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በተዛባ መልኩ ለተረዱ አንዳንድ የውጪ መንግስታት ምላሽ የምንሰጥበት ነው ብለዋል፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል የሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዚህ ዘመቻ መሳተፍና ድምጹን ማሰማት አለበት ብለዋል። 

ከዚህ በመነሳት በተለይም የአሜሪካ መንግስት እውነታውን ተረድቶ ሃሳቡን ያስተካክላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት" ብሄራዊ ንቅናቄ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተቀላቅለው ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም