ደጃዝማች ኡመር ሰመተር በአዲስ አበባ በስማቸው ትምህርት ቤት ተሰየመ

268

አዲስ አበባ መስከረም 14/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚገኘው እፎይታ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በደጃዝማች ኡመር ሰመተር ስም ተሰየመ።
የአዲስ ከተማ የክፍለ ከተማ የሥራ ኃላፊዎችና የሱማሌ ክልል ተወካዮች በተገኙበት መርሃ-ግብሩ ተከናውኗል።

የኦጋዴኑ የበረሃው መብረቅ ተብለው የሚታወቁት ደጃዝማች ኡመር ሰመተር ለእናት አገራቸው ነጻነት ከወራሪው የፋሽስት ጦር ጋር ከተዋደቁ ስመ-ጥር የኢትዮጵያ አርበኞች መካከል አንዱ ናቸው።

ደጃዝማች ኡመር ቆራሔ ላይ ጠላትን ገጥመው ድል ያደረጉ፤ ጠላት ምሽግ ገብተው የጨበጣ ውጊያ አካሂደው ጀብዱ የፈጸሙ ጀግና እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል።

በደጋሀቡር ከጦር አጋሮቻቸው ጋር ሆነው ፋሸስት ኢጣሊያን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው የላኩ ጀግና እና ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ መሆናቸው ይነሳል።

የወቅቱ የጦር አዛዦች ደጃዝማች ኡመር በተዋጉባቸው ቦታዎች ሁሉ ድል የሚያደርጉ፤ በተለይም በጎድሎጎቤ፣ ቆራሔና ሃለሌ በተባሉ ሥፍራዎች አስደናቂ ጀብዱ መፈጸማቸው ተሰንዶ ይገኛል።

አርበኛው ደጃዝማች ኡመር ሰመተር በአንድ ወቅት ''የአገሬን ህዝብ የፈጀው ጠላት በጀግኖች ክንድ ተረግጦ ሲወጣ በአይኔ ተመልክቻለሁ'' በማለት መናገራቸው ይነገራል።

ደጃዝማች ኡመር ሰመተር ከጠላት ጋር እየተፋለሙ በስድስት ጥይት ተመተው ከተዋጊነት መገለላቸውን ታሪክ ያትታል።

ጀግናው አርበኛ በተወለዱ በ65 ዓመታቸው መጋቢት 10 ቀን 1936 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸው በሀረር ከተማ ተፈጽሟል።

በመሆኑም እኒህ አገር ያኮሩ ጀግና የጀብድ ታሪካቸው በትውልድ ዘንድ ሲታወስ እንዲኖር እፎይታ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስማቸው መጠሪያ እንዲሆን ተሰይሟል።

ከዚህ ቀደም አንዋር መስጊድ አጠገብ በደጃዝማች ኡመር ሰመተር የተሰየመ ትምህርት ቤት የነበረ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቱ መፍረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም