የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የተለያዩ ምስጢራዊ ህትመቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ 14 የህትመት ማሽኖችን ሊገዛ ነው

95

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የተለያዩ ምስጥራዊ ህትመቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ 14 የህትመት ማሽኖችን ሊገዛ ነው።

ድርጅቱ የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት በማክበር ላይ ሲሆን የደም ልገሳ፣ ችግኞችን የመንከባከብ፣ የፓናል ውይይቶችና በሌሎች ኩነቶች ያከብራል ተብሏል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ፤ ድርጅቱ የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለባንክና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።      

ሆኖም ድርጅቱ የሚሰጠው የህትመት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ ረገድ የሚጠበቀውን ያክል ደረጃ ላይ አልደረሰም ነው ያሉት።       

ለዚህም ድርጅቱ የተለያዩ ምስጢራዊ ህትመቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ 14 የህትመት ማሽኖችን ለመግዛት በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ለ2014 ዓ. ም 515 ሚሊዮን ብር የካፒታል በጀት ድርጅቱ እንደተፈቀደለት ጠቁመው ከዚሁ ውስጥ 339 ሚሊዮን ብር ለህትመት ማሽኖች ግዥ የሚውል መሆኑን ጠቅሰዋል።  

የህትመት መሳሪያዎቹ ተገዝተው ስራ ሲጀምሩ ተጨማሪ ምስጢራዊ ህትመትን ጨምሮ በውጭ አገራት ይታተሙ የነበሩ በአገር ውስጥ እንዲታተሙ ይደረጋል ነው ያሉት።

የህትመት መሳሪያዎቹን ለመግዛት ጨረታ ወጥቶ አቅራቢ ተቋም መመረጡን አስታውሰው፤ ግዥውን ለመፈጸም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጥያቄ መቅረቡንም አመልክተዋል።  

የህትመት መሳሪዎቹ የድርጅቱን አቅም ከማሳደግ ባሻገር ጥራቱንም ከፍ ያደርገዋል ያሉት አቶ ሽታሁን ደንበኞች በሚፈልጉት ጊዜ የህትመት ውጤቶችን ተደራሽ ማድረግም ያስችለዋል ሲሉ ገልጸዋለ።

ድርጅቱ ከመደበኛ ስራው በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ለአገር መከላከያ ሰራዊትም 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።  

ድርጅቱ ባለፈው በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 161 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ አፈጻጸሙ 167 ሚሊዮን ብር መሆኑን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅቱ በሀገር ውስጥ የሚታተሙትን ምስጢራዊ ህትመቶችን ለ48 ዓመታት ያህል በብቸኝነት ሲያትም ቆይቷል።

ፔፐር አይዲ ካርድ፣ የፕላስቲክ ካርድ ህትመት፣ የሚፋቅ የሞባይል ካርድ፣ ክሬዲት ካርድ፣ የቅድመ ክፍያ ኤሌክትሮኒክስ ካርድ ህትመቶች ዋና ዋናዎቹ በምስጢራዊ ህትመት ሂደት ውስጥ የሚያልፉ የህትመት ውጤቶች መሆናቸውን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም