በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ኢንተርፕራይዞች መልሶ ለማደራጀት ትኩረት ይደረጋል

131

ባህር ዳር፣ መስከረም 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጓዳኝ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ኢንተርፕራይዞችን መልሶ ለማደረጀት ትኩረት እንደሚደረግ የፌደራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌዴራልና ክልል አመራሮች የተሳተፉበት የሥራ ዕድል ፈጠራ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በተስፋና በስጋት ውስጥ ሆና ባሳለፈችው 2013 ዓ.ም በሥራ ዕድል ፈጠራ የተሻለ አፈጻጸም ነበረ።

"በርካታ እንቅፋቶች ቢገጥሙም ችግሮችን በመቋቋም ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በወረራቸው አካባቢዎች የተገነቡ የሥራ እድል ፈጠራ ተቋማትን ማውደሙን የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ ድርጊቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴውን ፈተና ውስጥ እንዲገባ ያደረገው መሆኑን ተናግረዋል።

ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የሴቶች የስራ ዕድል ጠጠቃሚነት ድርሻ 35 በመቶ ብቻ በመሆኑ ሴቶች ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ነባር ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከርና ለአዳዲስ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር 3 ሚሊዮን ዜጎችን በዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል።

"የዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ የሁሉንም አካላት ጠንካራ ድጋፍና እገዛ ይፈልጋል" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ለዚህም ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው በክልሉ የህወሓት አሸባሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት ከ18 ሺህ 900 በላይ ኢንተርፕራይዞችና የቴክኒክ ሙያ ኮሌጆች መውደማቸውን ገልጸዋል።

"ሰላም ከማስከብሩ ተግባራት ጎን ለጎን የወደሙ ኢንተርፕራይዞችን፣ ከሥራ ውጭ የሆኑ ተቋማትን ማቋቋም ትልቁና የመጀመሪያ ስራ መሆን አለበት" ብለዋል።

ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ሥራ አጥ ዜጎችን በመመዝገብ ስራ ለማስያዝ ከባለድረሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል

ክፍት የስራ ቦታዎችን የመመዝገብና ሥራ ፈላጊውን የማገናኘት ሥራዎች በሚኒስቴሩ እንደሚከናወኑ ጠቅሰው፣ በተለይም በውጭ ሀገር የሥራ እድሎችን የማመቻቸት ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ከጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለ50ሺህ ዜጎች በውጭ አገራት የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሣኒ ረዲ ፈተና የበዛበት ያለፈው በጀት ዓመት የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ጥሩ አፈጻጸም እንደታየበት ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ የፋይናንስ እና የመሬት አቅርቦትን በማስተሳሰር በኩል የድርሻውን እንደተወጡም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም