በሚመሰረተው አዲስ መንግስት መዋቅር የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ፣ተስፋና አንድምታ

87

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) በሚመሰረተው አዲስ መንግስት መዋቅር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፍ የሰነቀው ተስፋና አገራዊ አንድምታ ፈርጀ ብዙ ነው ሲሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተናገሩ።

ባለፈው ውርኅ ሰኔ የተደረገው ስድስተኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ምርጫዎች በተለየ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ እንደሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይናገራሉ።

የፊታችን መስከረም 24 ቀን የሚመሰረተውን ለቀጣይ አምስት ዓመታት መንግስትን የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንደሚያሳትፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል።

ኢዜአ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት እንዳሉት፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በአዲሱ መንግስት መዋቅር ተሳታፊ ከተደረጉ የሚኖረው አገራዊ አንድምታ ፈርጀ-ብዙ ነው።

የራያ ራዩማ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ከበደ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የታቀፉ 46 ፓርቲዎች ጉዳዮቻቸውን በጋራ ምክር ቤቱ እያቀረቡ ምክክር ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በዚህም "በየወቅቱ አላስፈላጊ አመጾችና ሰልፎች ከመደረግ ተቆጥበዋል" ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ይህም የፓርቲዎች በሃሳብ የማመን እና የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋና እየሰለጠነ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስት መስከረም 24 ቀን አዲስ በሚመሰረተው መንግስት መዋቅር ውስጥ "ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደየተሳትፏቸው አሳትፋለሁ ማለቱ ለቀጣይ ሰላማዊ መንግስት ምስረታ ጉልህ ሚና ይኖረዋል" ብለዋል።

አገር የጋራ በመሆኗ ምርጫ ያሸነፈ ብቻ ሳይሆን ሌላው ፖለቲከኞች በተለያዩ ሙያዎችና ፖለቲካ ጉዳዮች መሳተፋቸው በሌሎች አገራትም የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የአገር እጣ ፈንታ ለመወሰን ያሸነፈ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ሌላውም ፓርቲ ካላስፈላጊ አመፃና ፉክክር ወጥቶ ሁሉም አካል እንደየሙያው ያለውን ሃሳብ አቅርቦ በጋራ መስራት አገራዊ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።

የሕዳሴ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ ሱራፌል እሸቱ፤ ፓርቲያቸው በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ መራጩ ህዝብ ይበጀኛልና የተሻለ ፕሮግራም አለኝ የሚለውን ፓርቲ መርጧል ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል።

መንግስት ለመመስረት ያሸነፈው ፓርቲ በአዲሱ መንግስት መዋቅር ውስጥ "የፖለቲካ ፓርቲዎችን አሳትፏለሁ" ብሎ ቃል መግባቱን አስታውሰው፤ ይህ የሁሉንም የተሻለ ሃሳብ በአዲሱ መንግስት ውስጥ ገቢራዊ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁልጊዜ መቃወም ብቻ ሳይሆን በአገራዊ ጉዳዮች አሻራቸውን የሚያሳርፉበት ዕድል የሚፈጥርም እንደሆነ ተናግረዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ ክፍለማርያም ሙሉጌታ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች አገር በመሆኗ በመንግስት መዋቅር አሳትፋለሁ ማለታቸውን አንድቀዋል።

ይህ ከሆነ በአገር ጉዳይ ሰፊ ልዩነት ያላቸውን ፖለቲከኞች ወደጋራ መግባባትና አንድነት እንደሚያመጣ ገልጸው፤ ይህም በተለይም ለአሁናዊ ችግሮችን ለማለፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖርው ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁሉም ፖለቲከኞች በአገራቸው ጉዳይ ወደአንድነት መጥተው ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ማሻገር እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም