የአዋሽ መልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በሄክታር 35 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረጉን ገለፀ

216

አዳማ፣ መስከረም 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዋሽ መልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በሄክታር 35 ኩንታል ምርት የሚሰጡ የቆላ ጥራጥሬ ሰብሎችን ምርጥ ዘር በምርምር አውጥቶ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረጉን ገለፀ።

ማዕከሉ የምርምር ውጤቶቹ ያመጡትን ለውጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በድሩ በሽር ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ስድስት አይነት የቦለቄ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚዎች እያደረሰ ነው።

በአውሮፓና እስያ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የቦሎቄ ዝርያዎች ላይ በትኩረት በመስራት ቀደም ሲል በሄክታር ከ10 ኩንታል የማይበልጠውን ምርት እስከ 35 ኩንታል ማሳደግ የሚያስችል ምርጥ ዘር መውጣቱን ተናግረዋል።

በማዕከሉ የጥራጥሬ ሰብሎች ተመራማሪ ዶክተር ብርሃኑ አምሳሉ በበኩላቸው ምርጥ ዘሮቹ በአርሶ አደሩ ማሳ በኩታ ገጠም በሰርቶ ማሳያ እየለሙ መሆኑን ገልጸዋል።

ቦለቄ ለውጭ ገበያ ከሚልኩ ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያና አርሶ አደሮች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ታደሰ እንደገለፁት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ቦሎቄና ስንዴ በመጪው በጋ በመስኖ ለማልማት ታቅዷል።

ለዚህ የሚሆን ምርጥ ዘር የአዋሽ መልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከልና በአርሶ አደሩ ማሳ እየተባዛ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግስት ማዕከሉ ለጀመረው የምርምር ስራ ውጤታማነት ተገቢውን ድጋፍና ዕገዛ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥራጥሬን ለዓለም ገበያ በአይነትና በጥራት ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ሞቱማ ቶሎሳ በበኩላቸው “ከማዕከሉ የተገኘ የቦለቄ ምርጥ ዘር በ11 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም እያባዛን እንገኛለን” ብለዋል።

ማዕከሉ በዞኑ አርሶ አደሩን በማስተባበር ለምርምር ውጤቶች ማስፋፊያ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢኮስ የቦለቄ ላኪ ድርጅት ተወካይ አቶ ሽመልስ ወርቅአገኘው እንደገለፁት፤ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የቦለቄ ዝርያዎች ላይ ማዕከሉ የምርምር ትኩረቱን እንዲያደርግ አብረው እየሰሩ ነው።

ተፈላጊ የሆኑ የቦሎቄ ዝርያዎች በስፋት ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ ከውጭ ዝርያዎችን በማስመጣት ጭምር ምርምር እንዲካሄድባቸው በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም