በፀጥታ ችግር ምክንያት ለተከሰቱ ውድመቶች የመልሶ ማቋቋም እና ልማት የተመድ ትብብር እና ድጋፍ ተጠየቀ

72

መስከረም 14 /2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በፀጥታ ችግር ምክንያት ለተከሰቱ ውድመቶች የመልሶ ማቋቋም እና ልማት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትብብር እና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ።

አቶ ደመቀ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሃፊ አሚና ጄኔ መሐመድ ጋር መክረዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እና የወደሙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት መንግስት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዘላቂ የልማት ግቦች አፈፃፀም፣ በሰብዓዊ አገልግሎት ድጋፍ አሰጣጥ እና ወቅታዊ የአገር ጉዳዮችን በተመለከተ አቶ ደመቀ ከተመድ ምክትል ዋና ፀሃፊ ጋር በዝርዝር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እና የወደሙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግስት በመልሶ ማቋቋም እና በመልሶ ማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሂደት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከተ.መ.ድ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።

በአሁን ጊዜ አገሪቱ እየገጠሟት ካሉት የፀጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ የመልሶ ማቋቋም እና የመልሶ ማልማት ተልዕኮን ለማስፈፀም በተመድ በኩል የበለጠ ትብብር እና ድጋፍ እንጠብቃለን ብለዋል አቶ ደመቀ።

በመጨረሻም እስካሁን ድረስ የተ.መ.ድ በልማት እና ሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ዙሪያ ለኢትዮጵያ ላበረከተው አስተዋፅዖ በማመስገን፤ በአሁን ጊዜ ወቅቱ የተሻለ ትብብርና መደጋገፍ እንደሚጠይቅ ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም