እየተቀዛቀዘ የመጣውን የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ማጠናከር ይገባል…ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

61
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010 የፕሮግራም ማሻሻያ በማድረግ በኢትዮጵያ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ማጠናከር እንደሚገባ የኢፌዴሪ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ። በአገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ ''የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በማጠናከር ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳካት'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው። የጤና ኤክስቴንሽን ማሻሻያ ፕሮግራምና የከተማ ጤና ንቅናቄ የጉባዔው ዋነኛ አጀንዳዎች ናቸው። በጉባኤው የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያስመዘገበች ላለው አመርቂ ውጤት የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በአሁኑ ወቅት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ አገልግሎቱን ማግኘት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በሚፈለገው ደረጃ ተደራሽ እየሆኑ አይደለም። በዚህም ባለፉት ዓመታት የተገኙትን ውጤቶች ለማስቀጠል ፕሮግራሙን በማሻሻል ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል። አገሪቱ በሁሉም መስኮች ለውጥ ለማምጣት እየተጋች ባለችበት ወቅት ዜጎች የኢኮኖሚ ደረጃቸውና የአኗኗር ዘይቤ እየተቀየረ መምጣቱን ተከትሎ ተላላፊ የሆኑ፣ ተላላፊ ያልሆኑና ከአደጋዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጤና እክሎች እየተስፋፉ መጥተዋል። በዚህም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን በማሻሻል ትግበራውን ከመጀመር ባሻገርም የከተማ ጤና ስትራቴጂን በተጠናከረ ሁኔታ ለማስፈጸምና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ  ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ፖሊሲ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችና የእናቶች ሞት ለመቀነስ በተደረገው ጥረት የጎላ አስተዋጥኦ እንደነበው ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ለጤና ኤክስቴንሽን የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ በመምጣቱ የፕሮግራሙ መቀዛቀዝ በታቀደው ልክ የዜጎችን የጤና ተደራሽነት ማረጋገጥ ላይ ክፍተት መፈጠሩን ጠቁመዋል። ለፕሮግራሙ መቀዛቀዝ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል ማነስ ቀዳሚ መንስዔ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አሚር ያሉትን ችግሮች በመለየት ፕሮግራሙን ማሻሻል ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ ማሻሻያ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ ያካሄደው የዳሰሳ ጥናት ከጉባዔው በሚገኝ ግብዓት ዳብሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አመልክተዋል። የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከተጀመረበት ከ1994 ዓ ም ጀምሮ አሁን እስከሚገኝበት ደረጃ ድረስ ምን እንደሚመስል የሚያስቃኝ ጽሁፍ ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ከበደ ወርቁ በአገሪቷ ከ39ሺህ878 በላይ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎ ሰልጥነው ከ16 ሺህ በላይ በሆኑ የጤና ኬላዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ፕሮግራሙ መተግበር ከጀመረበት አንስቶ በጤና ዘርፍ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግና ግንዛቤ በመፍጠር በበሽታ መከላከል ረገድ የላቀ ውጤት መምጣቱን ጠቁመዋል። ይህም ደግሞ በወሊድ ምክንያት የሚፈጠረው የእናቶች ሞት እ.አ.አ. በ1990 ከ100ሺህ እናቶች 1064 ይሞቱ ከነበረበት በ2016 ወደ 412፤ የህጻናት ሞትን ደግሞ ከ1ሺህ ህጻናት ይሞቱ ከነበሩት 244 ወደ 67 ዝቅ ማድረግ ተችሏል። በተመሳሳይም የኤችአይ ቪ ስርጭትን ደግሞ 90 በመቶ ያህል እንዲቀንስ አስችሏል። የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በሙከራ ደረጃ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የፕሮግራሙን ሂደት የሚያስቃኝ የፎቶ ኤግዚቢሺን ቀርቦ ተጎብኝታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም