በከተማው የመስቀል በዓል የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና በማሰብ ይከበራል

77

ጎንደር ፤ መስከረም 13/2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የዘንድሮ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ የአብሮነት እሴቶችን በጠበቀ መንገድ በአሸባሪው የህውሃት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በማካሄድ እንደሚከበር የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት አስታወቀ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በሰላም የመስቀል በዓል አንዲከበር ለማድረግ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ከከተማው የፀጥታ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርሲቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ዮሴፍ ደስታ ፤ የዘንደሮ የመስቀል በዓል ሀገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ይከበራል ብለዋል።

በዚህም ሃይማኖታዊ የአብሮነት እሴቶችን በጠበቀ መንገድ በወራሪው ህወሓት የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና በማሰብ በዓሉ እንደሚከበር አስታውቀዋል።

ወደ ደመራው ስፍራ የሚመጡ ምዕመናን ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ስጦታ የሚያበረክቱበት መርሃ ግብር በማካሄድ በዓሉ ቤተ-ክርስቲያኑዋ ለወገኖቿ የምትደርስበት እለት ሆኖ እንዲከበር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት።

በጎንደር ከተማና ዙሪያው የሚገኙ አብያተ-ክርስቲያናትና አድባራት ጭምር በነፍስ ወከፍ የድጋፍ መዋጮ እያካሄዱ መሆኑን ጠቁመው፤ በዕለቱ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደሚላክ ገልጸዋል፡፡

"በዓሉ ከልክ ባለፈ መዝናናትና ጭፈራ የምናከብረው ሳይሆን ሀገር ሰላም እንዲሆንና የህዝቦች ሰቆቃና መፈናቀል እንዲቆም በመስቀሉ ስም ፈጣሪን በፀሎትና በሃይማኖታዊ ስርዓት የምንለምንበት ነው" ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አስስተዳደር ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው ፤ የጎንደርን ሰላምና ደህንነት የማይፈልገው የህወሓት የሽብር ቡድን የጥፋት ተልዕኮውን ለማክሸፍ ከህብረተረሰቡ ጋር በመሆን ነቅተው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።  

"የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል በፈፀመው ወረራ በርካታ ወገኖቻችን በግፍ ተፈናቅለዋል፤ የእምነቱ ተከታዮች ለበዓሉ ድግስ የምናወጣውን ወጪ ለተፈናቀሉ ወገኖች በማዋል ለወገኖቻችን እንድረስላቸው" ብለዋል።

በየዓመቱ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት የሚከበረው የመስቀል በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ አስፈላጊውን የዝግጀት ሥራ ማጠናቀቁን  የገለጹት ደግሞ  የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ዋና ኢንስፔክተር ካሳው ጀንበር ናቸው ፡፡

በከተማዋ  ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ደመራው በሚለኮስበት ስፍራ የጦር መሳሪያ ይዞ መግባትም ሆነ መጠጥ ጠጥቶ ወደ ስፍራው መምጣት ክልክል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የከተማዋ  የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የአስተዳደሩ  አመራሮች፣ የፀጥታ ሃይሎችና የወጣት አደረጃጀት መሪዎች ተሳትፈዋል 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም