በየመንገዱ ዳር የሚጣለው ደረቅ ቆሻሻ በጤናችን ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው - የሀረር ከተማ ነዋሪዎች

145
ሃረር ነሀሴ 9/2010 በሐረር ከተማ በየመንገዱ ዳር የሚጣለው ደረቅ ቆሻሻ በጤናቸው ላይ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ። በሆቴል ስራ የሚተዳደሩት አቶ ጸጋዬ ብርሃኑ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት  በአካባቢያቸው በዘፈቀደ የሚጣለው ደረቅ ቆሻሻ በሆቴል ስራቸውም ላይ ሆነ በሰራተኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጤንነት ላይ  ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡ ''ጉዳዩን አስመልክተን ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ የሚሰጥ አካል ልናገኝ አልቻልንም'' ብለዋል፡፡ ቆሻሻው የሚያነሳ አካል ባለመኖሩ አካባቢው ለጤና ችግር መንስኤ እየሆነ ነው፤ እኔም የአስም በሽተኛ አድርጎኛል ያለው ደግሞ በአነስተኛ ሸቀጥ ንግድ የተሰማራው ወጣት አለማየው ሙላቱ ነው፡፡ ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለሚገኝ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡ በጫኝና አውራጅ ስራ የተሰማራው ወጣት ሔኖክ አስፋው ’’በከተማው ትልቁ ሸዋ በር ገበያ አካባቢ ቆሻሻ ይጣላል፤ በዚህም በስራችን ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው፤ እኛ ከህመም ጋር እየተሰቃየን ስንሰራ ሌሎች ግን ስራውን ለመተው ተገደዋል’’ ብሏል። በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ የተሰማሩት አቶ አበበ ሐይሉ በበኩላቸው ''አትክልት ከቆሻሻው አጠገብ ይሸጣል ይህ ደግሞ  በጤና ላይ ችግር እየፈጠረ ነው፤ መንግስት አለ ለማለት ያስቸግራል፤ አሁን አሁን ግን ሁኔታው እየተባበሰ ስለሚገኝ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል'' ብለዋል፡፡ ቆሻሻው በጀጎል ዙሪያም በመባባሱ ለጎብኝዎችም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን የገለፁት አስተያየት ሰጪዎቹ ቆሻሻው የመኪና መንገድ ላይ ጭምር ስለሚደፋ አሽከርካሪዎች በተጨናነቀና ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ በመጓዝ  ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ በከተማው የቆሻሻ አወጋገድ ችግር ዙሪያ ቀደም ሲል ኢዜአ ተደጋጋሚ ዘገባዎችን መስራቱ ይታወሳል፡፡ አሁንም በከተማው ቢራ ሰፈር፣ ሸዋ በር የገበያ ስፍራ፣ ቡቴ፣ ሸንኮር ወረዳና  ሌሎች ስፍራዎች ላይ በየመንገዱ ዳር ለበርካታ ጊዜ የተጠራቀመ  ደረቅ ቆሻሻ የኢዜአ ጋዜጠኛ ተመልክቷል። በጉዳዩ ዙሪያ የከተማውን ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ሙሐመድ ኑረዲንን ለማናገር በተደጋጋሚ ወደ ቢሮአቸው በመሄድና በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ''በክልሉ የቆሻሻ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቷል፤ ህብረተሰቡም እያነሳ ያለው ቅሬታ ትክክልና እግባብነት ያለው ነው'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም ናቸው፡፡ በክልሉ 60 በመቶ በሽታ የሚከሰተው ከግልና ከአካባቢ ንጽህና ጉድለት ነው ይህም እኛን እያሳሰበን ይገኛል። በቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ህብረተሰቡም እያከናወነ የሚገኘው የቆሻሻ አወጋገድ ሁኔታ በራስ ጤና ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል የቆሻሻ አወጋገድ ባህሉን እንዲያሻሽል ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም