ሴት ነጋዴዎች ለዘርፉ እድገት ሚናቸውን እንዳይጫወቱ የገንዘብ አቅርቦትና ሌሎች ችግሮች እየገጠሟቸው ነው ተባለ

67
አዲስ አበባ ነሀሴ 9/2010 ኢትዮጵያ ውስጥ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ነጋዴዎች ለዘርፉ እድገት ተገቢውን ሚና እንዳይጫወቱ የገንዘብ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑን ገለፁ። ሴቶች በንግዱ ዘርፍ ጠንካራ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ለማድረግ መንግስት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ተገልጿል። ይህ የተገለፀው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ባዘጋጀውና ሴት ነጋዴዎች በሥራ እንቅስቃሴዎቻቸው በሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ላይ በመከረው የውይይት መድረክ ነው። መድረኩ ከንግድ ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎች፣ ህጎችና ማዕቀፎችን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ ችግሮች ላይም ተወያይቷል። የንግድ እንቅስቃሴ መጠናከር ለአጠቃላይ አገራዊ እድገት ዋና መሰረት መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ዘርፉ በተለያዩ ማነቆዎች ሳቢያ የሚፈለገውን እድገት እያመጣ እንዳልሆነም ተነግሯል። የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉትም በተለይ የገንዘብ፣ የቦታና ሌሎች መሰረታዊ የንግድ ልማት ግብአቶች አቅርቦት እጥረት ለዘርፉ እድገት ማነቆ ሆኗል። በመሆኑም የንግድ ዘርፉን በማሳደግ አጠቃላይ አገራዊ የምጣኔ ኃብት ልማትን ማረጋገጥ እንዲቻል የግብዓት አቅርቦትን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት የሚታዩትን የፖሊሲ፣ ህግና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት ጥረት መደረግ እንዳለበትም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል። በተለይም በዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባም ገልጸዋል። በምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፍ የተሰማሩት ወይዘሮ ማህደር አድማሴ እንደሚሉት ሴቶች በዘርፉ ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚደረገው ድጋፍ አናሳ ነው። ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የመጡት ወይዘሮ እማዋይሽ መለስ በበኩላቸው በተለያዩ ወቅቶች የሚወጡ ህጎችና ፓኬጆች በተሟላ መልኩ ስራ ላይ ካለመዋላቸው ጋር ተያይዞ በዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል እድገት እንዳይመጣ እንቅፋት እየሆነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በመሆኑም የብድር አቅርቦትን ጨምሮ ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ህጎች፣ አሰራሮችና ማዕቀፎችን ተግባራዊ የማድረግ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው በሴት ስራ ፈጣሪዎች የሚመሩ ኢንተርፕራይዞች ለዘርፉ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። ሴቶች ለዘርፉ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው ቢሆንም በገንዘብ፣ በግብአት በቦታ እጥረት፣ እንዲሁም ፖሊሲዎችና አሰራሮች በትክክል ተግባራዊ መሆን ባለመቻላቸው ተገቢውን እድገት ሊያስመዘግቡ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ችግሮቹ ተቀርፈው ሴት ነጋዴዎች ለአገር እድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ፖሊሲዎችና ህጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ፤ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ምክር ቤቱ የበኩሉን እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም