ትውልድን በእውቀትና በስነ-ምግባር በማነጽ የሃገር እድገት ግብን ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ ነው…ትምህርት ሚኒስቴር

68

መቱ መስከረም13/2014 (ኢዜአ) የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን በዕውቀት፣ በክህሎትና አመለካከት በማነጽ የሀገራቸውን ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲያሳኩ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ጀምሮ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የተመራ የልኡካን ቡድን ሚኒስትሩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩበትን ሀሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጨምሮ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ጎብኝቷል።

በሀገራችን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከነበሩበት ሁኔታ በማሻሻልና ግብዓቶችን በየደረጃው በማሟላት ለመማሪያነት ምቹ ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ጥራት ባለው ትምህርት በዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በማነጽ የሀገራቸውን ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲያሳኩ ለማስቻል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ጀምሮ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉበት የሀሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በወረዳው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች መቀመጫና የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍም አበርክተዋል። 

በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ምቹ ባልሆኑ ሁኔታዎችና ደረጃቸውን ባልጠበቁ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተምረው ዓላማቸውን ያሳኩ በመሆኑ የዛሬው ትውልድም የትኛውም ዓይነት ችግር ሳይበግረው ተምሮ ለስኬት እንዲበቃ መክረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ገላና ወልደሚካኤል በበኩላቸው “በ2013 በጀት ዓመት ለክልሉ ከትምህርት ሚኒስቴር በተመደበ ከ400ሚሊዮን ብር በላይ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል፣ የመማሪያ ቁሳቁስ የማሟላትና አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ሥራዎች ተከናውነዋል” ብለዋል። 

እነዚህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል ዋና ዋናዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

“በክልሉ ሁሉም ዞኖች በባለሀብቶች፣ በሕብረተሰቡና በመንግስት በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ለብዙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ገልፀው ይህም ለተማሪዎች ተሳትፎና የትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትልቅ ድርሻ አለው” ብለዋል።

የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ነጋሽ “ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ባደጉበት ማህበረሰብ ውስጥ ገብተው ያሉትን ችግሮች የማየትና እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችን የመጎብኘት ተግባራት ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው” ብለዋል።

በዞኑ በትምህርቱ ዘርፍ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማጠናከር ለተደረጉ ድጋፎችም አመስግነው ሥራዎቹን ውጤታማ በማድረግ ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት ለመስኩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

በሚኒስትር ዲኤታው የተመራው ቡድንም በጉብኝቱ በመቱ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ችግኝ ተክሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም