በ253 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው የመንዲ ጊዳሜ የኤሌክትሪክ መስመር አገልግሎት መስጠት ጀመረ

66
መንዲ ጊዳሜ ግንቦት 8/2010 ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድርና በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ በ253 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የመንዲ ጊዳሜ የ150 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያና ማሰራጫ ጣቢያ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። አዲሱ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ካለፈው መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ ለአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ይህ ባለ 132 ኪሎ ቮልት አዲስ የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ የጊዳሜ ከተማን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው የገጠር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል። የመንዲ ጊዳሜ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት መሃንዲስ አቶ ሁሉንአየሁ ደጀኔ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ በ2003 ዓ ም ተጀምሮ በ2010 ዓ ም ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠው ጠቀሜታና የሚፈጥረው መነቃቀት ከፍተኛ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለጹት። ግንባታው ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድርና በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። የመንዲ ጊዳሜ ኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ልዑል በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የጊዳሜ ከተማና አካባቢዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል። በዚሁ መሰረት የመንዲ ጊዳሜ የሃይል ማስተላለፊያና ማሰራጫ ጣቢያ የሙከራ ስራ ከተከናወነ በኋላ ለብዙ ጊዜያት የኤሌክትሪክ ሃይል ሳታገኝ ለቆየችው የጊዳሜ ከተማ የሙሉ ጊዜ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንድታገኝ መደረጉን ተናግረዋል። በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችም ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከዚህ በፊት ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለማስቀረት ፕሮጀክቱ በጥራት የተሰራ መሆኑን የተናገሩት ስራ አስኪያጁ በእንጨት ይሰሩ የነበሩ ምሰሶዎችን ሙሉ በሙሉ በኮንክሪት ፖል መቀየራቸውን ገልጸዋል። ከተቀመጡት ሃያ ስድስት ትራንስፎርመሮች መካከል ሃያ ሶስት የሚሆኑት ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውን ጠቁመዋል። በተጨማሪም መንዲ ከተማ ላይ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የማስፋፊያ ስራ በመስራት በአካባቢው የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። የማስፋፊያ ስራው የጊዳሜ ከተማን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙት አለም፣ ግራይ ሰንቋ፣ ገባ ፈጫሳ፣ ቄለም እና አበቴን የተባሉት የገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል። አገልግሎቱን ለማዳረስ የመስመርና የኔትወርክ ግንባታ ስራው ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም