የደረቅ ብትን ጭነት ዘርፍ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

51

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13/2014(ኢዜአ)በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የገቢ እቃዎች 30 በመቶ ድርሻ ባለው የደረቅ ብትን ጭነት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶክተር ሹሜ በርሄ ተፈራርመዋል።

የደረቅ ብትን ጭነት ማዳበሪያ፣ ስንዴ፣ ስኳርና መሰል በብትን መልክ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ቁሳቁስ ወደብ ላይ ሲደርሱ ታሽገው የሚጓጓዙበት የጭነት አይነት ነው።

በስምምነቱ መሰረት የደረቅ ብትን ጭነት ላይ ያተኮረ ጥናት በማካሄድ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶች ከግማሽ በመቶ በላይ መፍታት እንደሚቻል ተገልጿል። 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ የደረቅ ብትን ጭነት ከአጠቃላይ የአገሪቷ የገቢ ንግድ 30 በመቶ ድርሻ እንዳለውና በኮንቴይነር፣ በወጪ ንግድና ሌሎች ጭነቶች ላይ ጫና እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በደረቅ ብትን ጭነት ላይ የመርከቦች በወደብና በባህር ላይ መዘግየት ችግር እንደሚስተዋል፤ የመርከቦች የባሕር ላይ ቆይታም እስከ ሶስት ወር ይደርስ እንደነበር አንስተዋል።

ይህ አካሔድ በሎጂስቲክስ ስርዓት ላይ የሚያስከትላቸውን ችግሮች በመለየት የአገሪቷን የደረቅ ብትን ጭነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ፅህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታዬ በበኩላቸው በተያዘው ዓመት ከ3 ሺህ በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች ግዥ በማከናወን የዘርፉን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከአገሪቷ የብትን ጭነት አስመጪዎች 80 በመቶዎቹ የመንግስት ድርጅቶች ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ አደረጃጀታቸውና የዕቅድና የግዥ ስርዓታቸው የተበታተነ መሆኑ በመርከቦች ቆይታ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የሚካሄደው ጥናት የተቋማቱን አሰራርና አደረጃጀት በመፈተሽና መፍትሄ በማመላከት በአገር አቀፍ ደረጃ ከግዥ እስከ መርከብ መረጣ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታ ታምኖበታል ብለዋል።

በደረቅ ብትን ጭነት ዘርፍ የሚያጋጥሙ የመጫንና የማራገፍ ችግሮች ለመፍታት በተከናወኑ ተግባራትም ሶስት ቀን ይወስድ የነበረውን የባቡር ጉዞ ወደ 1 ነጥብ 6 ቀን መቀነስ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ለሚቀጥሉት ስምንት ወራት የሚካሔደው ጥናት አምስት ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን ወጪው በኢትዮጵያ የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን እንደሚሸፈንም አክለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገሪቷን እድገት ለመደገፍ በተለያዩ ፕሮጀክቶች በመሳተፍ አበርክቶ እያደረገ መሆኑን የገለፁት የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶክተር ሹሜ በርሄ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ ለተቋማት የማማከር አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቅሰው በሎጂስቲክስ ዘርፍ ለሚያካሂደው ጥናት የተሰጠውን ኃላፊነት እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።

በጥናቱ ደረቅ ብትን ጭነት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ ውጤታማ ስራ መስራት የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦች ይቀርባሉ ብለዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የማሪታይምና ሎጂስቲክስ ሪፖርት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም