የ''ሄር ኢሴ'' ባህላዊ ህግ በአለም ቅርስነት ለማስመዘገብ እንቅስቃሴ ተጀመረ

86

ድሬዳዋ፤ መስከረም 13/2014(ኢዜአ) ''ሄር ኢሴ'' የኢሣ ማህበረሰብ ባህላዊ ያልተጻፈ ህግ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣የሣይንስና የባህል ድርጅት/ዩኒስኮ/ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ፣የጅቡቲና የሶማሌ ላንድ የኢሣ ማህበረሰብ አባቶች የተሣተፉበት በባህላዊ  ህጎች ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በድሬደዋ ተካሂዷል።

የሲቲ ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን ኃላፊ ወይዘሮ አያን አሊ በወቅቱ እንዳሉት፤ ''ሄር ኢሴ''  ባህላዊ መተዳደሪያ ህግ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን በ16ተኛው ክፍል ዘመን 44 የኢሣ  ማህበረሰብ አባላት ተቀምጠው ያጸደቁት ነው፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሶማሌ ህዝብ አንድ አካል የሆነው ኢሣ ማህበረሰብ ህጉን  ከትውልድ  ወደ ትውልድ በቃል እየተቀባበለ እየተመራበት እንደቆየ አስረድተዋል።

ህጉ በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሶማሌ ላንድ የሚገኙትን የማህበረሰቡን አባላት ያስተሳሰረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባህላዊ ህጉ ሀገራችን ለምትገነባው የዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግብአትነት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በአለም ቅርስት እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ አያን፤ ቅርሱ  ሲመዘገብና ሲተዋወቅ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራTን  ይበልጥ ያስተሣስራል ነው ያሉት።

የማህበረሰቡን ባህላዊና ታሪካዊ የጋራ እሴቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ ለቱሪስት መስህብነት በመዋል በጋራ  የማደግ ራዕይን እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የሚዳሰሱ ቅርሶችን በአለም አቀፍ ቅርስነት ማስመዝገብ የሚያስችል ሰነድ ዋና አዘጋጅ አቶ ገዛኻኝ ግርማ በወቅቱ እንደገለጹት፤    ባህላዊው ህግና ስርዓቱ በትውልድ ቅብብሎሽ እየዳበረ የመጣ ነው።

ባሀላዊ ህጉ እኩልነትን፣ሰው በሰውነቱ የሚከበርበትና የሚተዳደርበት የመቻቻልና የሰላም  እሴቶችን በውስጡ ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።

የሚፈጠሩ ችግሮችን በዛፍ ጥላ ሥር  በውይይት በመፍታትና በመከላከል ያበረከተው  አስተዋጽኦ የሚደንቅ ነው ብለዋል፡፡

ህጉን በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ያስታወቁት አቶ ገዛኻኝ፤የሚካተቱ ሌሎች ጉዳዮችን በማጠናቀቅ በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት  ለ"ዩኔስኮ" እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

የቅርሱ መመዝገብ የተሻለ ጥበቃና እንክብካቤ  ከማድረግ ባለፈ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ህዝብን የባህል ትስስርና ጠንካራ ወዳጅነት ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም