ኩባንያው በጋምቤላ ክልል ለ1 ሺህ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሶችን አበረከተ

83

ጋምቤላ ፤መስከረም 13/2014(ኢዜአ) ኢትዮ ቴሌኮም በጋምቤላ ክልል የመማሪያ ቁሳቁስ ለመግዛት አቅም ለሌላቸው 1 ሺህ 500 ህፃናት የትምህርት ቁሶችን አበረከተ።

ኩባንያው ድጋፍ ያደረገው ከ587 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 18 ሺህ የመማሪያ ደብተሮች መሆኑን በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ተመልክቷል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጅት በሥነ ሥርዓቱ ላይ፤ ድጋፉ በመማሪያ ቁሳቁስ እጦት ትምህርት የሚያቋርጡ ህፃናትን ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

በኩባንያው የታየው መልካም ተግባር በሌሎችም ተቋማት ሊለመድ ይገባዋል ብለዋል።

ድጋፉ ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በክልሉ ወረዳዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ለመግዛት አቅም ለሚያንሳቸው ህፃናት እንደሚሰራጭ ኃላፊው አስታውቀዋል።

በኢትዮ -ቴሌኮም የደቡብ ምዕራብ ምዕራብ ሪጅን የኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ አወል አብደላ፤ ኩባንያው ዘመናዊ የቴሌኮም አገልግሎቱን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ተማሪዎችን በትምህርት በመደገፍ ትውልድን የመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ኩባንያው በቀጣይም ዘርፉን ለመደገፍ በተያዘው የትምህርት ዘመን በክልሉ ሶስት ወረዳዎች በዘመናዊ ዲጂታል የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከክልሉ ድጋፍ ውስጥ በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ 150 ህፃናት በነፍስ ወከፍ  አንድ ደርዘን የመማሪያ ደብተር ተበርክቶላቸዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም