የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ተጠየቀ

62
አዲስ አበባ ነሐሴ 9/2010 የቱርክ ባለኃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ በማፍሰስ በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሳተፉ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ፋቲህ ዩሉሶይ ጥሪ አቀረቡ። አምባሳደሩ ጥሪውን ያቀረቡት በቱርክ አንካራ እየተካሄደ ካለው አስረኛው የአምባሳደሮች ጉባኤ ጎን ከአናዶሉ የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው። አምባሳደሩ ለዜና አገልግሎቱ እንደገለጹት፤ በመንግስት ይዞታ የሚተዳደሩ የልማት ኩባንያዎችን ወደግል ለማዞር የኢትዮጵያ መንግስት ሊተገብረው ባሰበው የፕራይቬታይዜሽን መርኃ-ግብር የቱርክ ባለኃብቶች በስፋት መሳተፍ እንዲችሉ ጉዳዩን በቅርበት መከታተል አለባቸው። አዲስ አበባ የሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተመተባበር ለቱርክ ባለኃብቶች በኢንተርኔት የታገዘ የቪዛ አገልግሎት መጀመሩን አምባሳደሩ ጠቁመዋል። በዚህም የቱርክ ባለኃብቶች ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን ሳያናግሩ የቪዛ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ገልፀዋል። የቪዛ አገልግሎቱን ለማጠናቀቅ ሦስት ቀናት እንደሚፈጅና አውደ ርዕዮችም ላይ ለመሳተፍ እድል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። ቱርክ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ጠናካራ አጋርነት እንዳላት የገፁት አምባሳደር ፈቲህ  በተለይም ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ሁለቱ አካላት በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። በመጪው 2011 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ የቱርክ-አፍሪካ የንግድ እና ኢኮኖሚ ፎረም በቱርኳ ኢስታንቡል ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድም አምባሳደሩ ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም