በሀገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል - የሰግለን ኢሉ አባገዳዎች ጉባኤ አባላት

122
መቱ ነሃሴ 9/2010 በሀገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት የሰግለን ኢሉ አባገዳዎች ጉባኤ አባላት ገለጹ፡፡ የአባገዳዎች ጉባኤ አባላቱ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ በሀገሪቱ የተመዘገበው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተለይ ወጣቱ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የሰግለን ኢሉ አባገዳዎች ጉባኤ ጸሀፊ አባገዳ ተሰማ ሙሉነህ እንዳሉት ወጣቱ ባደረገው ትግል መላው ህብረተሰብ የተደሰተበት ለውጥ ተመዝግቧል፡፡ ''እየተገኘ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በህብረተሰቡ መካከል መደማመጥ ያስፈልጋል'' ብለዋል፡፡ ''ሀገሪቱ የተለያዩ ሀይማኖቶች ተከባብረው የሚኖሩባትና በአለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅ ናት'' ያሉት አባገዳው በአንዳንድ አካባቢዎች የአልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን የሚቀሰቅሱ አካላትን ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የኦሮሚያ አባገዳዎች እና የሰግለን ኢሉ አባገዳዎች ምክር ቤት አባል አቶ ሀይሉ ለገሰ ቤኮ በበኩላቸው በሀገሪቱ አሁን የሚታየውን ለውጥ ለማስቀጠል በተለይ አመራሩ የለውጥ አመራር ሊሆን ይገባል፡፡ ''ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኩል ውስንነት ይታያል'' ያሉት አቶ ሀይሉ አመራሩ የህዝቡን ጥያቄዎች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ መፍታት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የገዳ ስርአት ግጭትና ያለመግባባትን ለመቅረፍ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸው በአሁኑ ወቅትም በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለውን ችግር በውይይት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የሚጥሩ ሀይሎችም ወደ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በመምጣት የሀገሪቱን ሰላም፣ ልማትና እድገት  እንዲያስቀጥሉ አባገዳዎቹ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም