የኢሬቻ በዓልን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው

91

ጭሮ፤ መስከረም 12/2014(ኢዜአ) የእርቅ፣ የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር በዓል የሆነው ኢሬቻን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የዞኑ  አስተዳደር ከአባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በበዓሉ አከባበር ዝግጅት ዙሪያ ውይይት አካሄዷል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር ተወካይ  አቶ አብዱራህማን ሁቤቢ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፤ ህዝቡ ኢሬቻን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲያከብረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በየደረጃው ተካሄደዋል።

የእርቅ፣ የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና የወንድማማችነት በዓል የሆነው ኢሬቻ  በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር  ህዝብን ያሳተፈ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የኢሬቻ በዓል  የኦሮሞ የገዳ ስርዓትና ባህል በሚያሳይ መልኩ በሰላማዊ ሁኔታ ለማክበር የሁሉም ህብረተሰብ የጋራ ትብብር እንደሚያሻው  አቶ አብዱራህማን ተናግረዋል፡፡

የጭሮ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ተቋማት አማካሪ  አቶ ከማል መሐመድ ፤ ህብረተሰቡ የአንድነት፣ የሰላምና የደስታ በዓል የሆነውን ኢሬቻን ሲያከብር በሀገሪቱ እየተስፋፋ ካለው  የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን እራሱን መጠበቅና ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ 

ፀጥታን በማስከበር ዙሪያ  ከአባገዳዎችና ሀደሲንቄዎች ጋርም መወያየታቸውን የገለጹት አቶ ከማል፤ ወጣቶች በዓሉ በሰላም እንዲከበር አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ትልቅ ድርሻ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በርካታ ተሳታፊዎች የሚታደሙበትና ትልቅ ባህላዊ እሴት ማሳያ ሆኖ እንዲከበር ቅድመ ዝግጅቱ እየተገባደደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  የጭሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ እስክንድር አህመድ ናቸው።

ዓላማውም የኦሮሞ ህዝብ የክረምቱን ጊዜ አሳልፎ  ወደ በጋው ስላሸጋገረው ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ የሚያከብረው ደማቅ በዓል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ኢሬቻ ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚከበርና የኢትዮጵያ መድመቂያ እንዲሆን ሁላቸውም  የባህል ልብሳቸውን ለብሰው እንዲያከብሩ  ተጋብዘዋል ብለዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ  ሀሊማ አብዱሰላም በሰጡት አስተያየት ፤የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓልን የሐረርጌን  ባህል በሚያንፀባርቁ ውብ አልባሳት ደምቀው ለማክበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከአካባቢ የፀጥታ አካላት ጋር በመስራት በዓሉን በሰላም ደምቆ እንዲከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የኦሮሞ  መገለጫ ሆኖ የቆየው የእሬቻ በዓል  እንደ አጠቃላይ መስከረም 22/2014ዓ.ም. በአዲስ አበባ(ሆረ ፊንፊኔ) እና መስከረም 23 ደግሞ ቢሾፍቱ ( ሆረ አርሰዲ)በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም