ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ ነው

51

ደሴ  መስከረም 11/2014 /ኢዜአ/ ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በመጠቀምና ሰብሉን በመንከባከብ የግብርና ምርቱን ማሳደግ ይጠበቅበታል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ አሳሰቡ።
 በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዳዋ ጨፋ ወረዳ በተሻሻለ ሰብል ዝርያ ለአርሶ አደሩ ሰርቶ ማሳያ የለማ ሰብል ጉብኝት ተካሒዷል።

በጉብኝቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሃት የከፈተብንን ጦርነት በመመከት ህልውናችንን ከማስቀጠል ጎን ለጎን የመኸር ሰብሉን መንከባከብና ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ተጠቅሞ ምርታማ እንዲሆንና የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዳዋ ጨፋ ወረዳ ሰርቶ ማሳያ ጣቢያ የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት በተግባር እያሳየ ነው” ብለዋል።

“በሰርቶ ማሳያው የለሙ ሰብሎች ምርት ለቀጣይ ዘር እንዲሆን ለሞዴል ለአርሶ አደሮች እንደሚሰራጭ ጠቁመው፤ሞዴል አርሶ አደሮች ደግሞ ለሌሎች አርሶ አደሮች ዘር እንዲሰጡ ይደረጋልም” ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ዲን ዶክተር አሊ ሰይድ በበኩላቸው እንደገለጹት በጣቢያው በሁለት ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ በምርምር የተገኙና የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ ሰብሎችን በሰርቶ ማሳያነት እየለማ ነው ፡፡

ዝርያቸው በሽታን መቋቋም የሚችሉ፣ ባጠረ ጊዜ ምርት መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ቡቃያው በጥሩ ሁኔታ ላይ በመሆኑ ቀጣይ ለአርሶ አደሩ ዘር ተሰጥቶ በብዛት እንዲመረት እንደሚደረግም ገልፀዋል።

በሰርቶ ማሳያ እየለሙ ያሉት ሰብሎች የማሾ ፣ የጤፍ፣ የማሽላ፣ የበቆሎ፣ የቦሎቄና የስንዴ ምርጥ ዘሮች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እነዳለውም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በምስራቅ አማራ ከሚገኙ ግብርና ባለሙያዎችና ከአመራሩ ጋር በቅንጅት የተጀመሩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ማባዛት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። 

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ በሬሳ ረጋሳ አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ ለማምረት የሚያርገው ጥረት ውጤታማ ባለመሆኑ በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻሻሉ ዝርያዎችን እንዲጠቀምና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ታግዞ የጀመረው ሰርቶ ማሳያ ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ተስፋን የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

“ዘንድሮ የለማውን ምርት በመሰብሰብ ዘሩን ለሞዴል አርሶ አደሮች በማሰራጨት በቀጣይ የመኸር ወቅት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል” ብለዋል።

በዳዋ ጨፋ ወረዳ የበደኖ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኢብራሒም ሙሄ በሰጡት አስተያየት በባህላዊ መንገድ የሚለያሙት ማሽላና በቆሎ ረጅም ጊዜ ከመውሰዱም ባለፈ ምርታማነቱ አነስተኛ በመሆኑ በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም ነበር።

በዩኒቨርሲቲው ሰርቶ ማሳያ ጣቢያ የለማው ግን በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጥና በሽታን መቋቋም የሚችል መሆኑን በተግባር እያዩ በመሆኑ በሚቀጥለው ዓመት የዚህን ዘር ተጠቅመው አንድ ሄክታር መሬት ለማልማት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

“በባህላዊ መንገድ ከሚያመርቱት ማሽላ ከአንድ ሄክታር ከ20 ኩንታል በታች ምርት ያገኙ እንደነበረ ጠቁመው፤ አዲሱ ዝርያ እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ በጥናትና ምርምር መረጋገጡን ከግብርና ባለሙያዎች ተገንዝበናል” ብለዋል። 

በጉብኝቱ የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ የደቡብ ወሎ ዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች፤ ሞዴል አርሶ አደሮችና ባለድሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም