በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ባለፈው የበልግ ወቅት ያጋጠመውን የምርት ጉድለት ለማካካስ እየተሰራ ነው

63

ሀዋሳ ፤ መስከረም 11/2014(ኢዜአ) ባለፈው ዓመት የበልግ ወቅት ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት የተጓደለውን በመሀር ምርት ለማካካስ እየተሰራ መሆኑን የደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች የግብርና ሴክተር ኃላፊዎች አስታወቁ።
የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት ፤የ2013 ዓ.ም የበልግ ወቅት እርሻ ሥራ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ተደርጎ የተገባበት ቢሆንም በወቅቱ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት የተዘራው ያልበቀለባቸውና ደርቆ የቀረባቸው አካባቢዎች በርካታ ናቸው።

በዚህም  ከ35 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምርት ጉድለት እንዳጋጠመ  ጠቅሰዋል።

ጉድለቱን በ2013/14 የመኸር ወቅት  እርሻ ለማካካስ ከዚህ በፊት ይለማ ከነበረው 154 ሺህ ሄክታር  ተጨማሪ ማሳ በሰብል የመሸፈን ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ አንተነህ እንዳሉት፤ ምርታማነትን የሚጨምሩ ግብዓትና ቴክኖሎጂ የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።

የአካባቢዎችን የማምረት አቅም በመለየትና የኩታ-ገጠም እርሻን በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ አምና 50 በመቶ የነበረውን የኩታ-ገጠም እርሻ 70 በመቶ ማድረስ መቻሉን አመልክተዋል።

በዘር የተሸፈነ ማሳ የመንከባከብ እንዲሁም ከአረምና በሽታ የመከላከል ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ በክልሉ በበልግ ወቅት ምርት ያልሰጡ ማሳዎች በመኸር ሰብል እንዲሸፈኑ ተደርጓል ብለዋል።

ለአርሶ አደሮች የሚያስፈልገው ግብዓት በየአካባቢው ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የልማት ድርጅቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ማሟላት መቻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ በ2013/2014 የምርት ዘመን   6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የማልማት ስራ እየተካሄደ መሆኑንና ይህም ከቀዳሚው ዘመን ብልጫ እንደሚኖረው ነው ያመለከቱት።

በበልግ የታየውን ጉድለት ለማካካስ ቀደም ባለው ዘመን  የነበረውን 169 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የመኸር ምርት ወደ 198 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን  ከክልሎች የሴክተርና ተጠሪ ተቋማት ሀላፊዎች ጋር በመሆን በደቡብ ክልል በከምባታ ጠምባሮና ስልጤ ዞኖች የግብርና እንቅስቃሴን በመስክ  መመልክታቸውን ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም