በሪጅኑ የአራተኛው ትውልድ የሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጠቀሜታው የጎላ ነው

75

ነቀምቴ ፤ መስከረም 11/2014(ኢዜአ) በኢትዮ-ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን የአራተኛው ትውልድ /4ጂ/ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ ፈጣን የሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎት ማስጀመሩ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ አስታወቁ።

የአራተኛው ትውልድ ፈጣን  የሞባይል  ኢንተርኔት አገልግሎት የደምቢዶሎ፣ ነቀምቴ፣ ጊምቢ፣ ባኮ እና ሻምቦ ከተሞች የሚገኙ ከ256 ሺህ በላይ ደንበኞች ተጠቃሚ ያደርጋል። 

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋናሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በወቅቱ እንዳስታወቁት፤ አገልግሎቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ጠቀሜታው የጎላ ነው።

የአራተኛው ትውልድ   የሞባይል ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ለአካባቢው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ማደግ ትልቅ ድርሻ የሚኖረው ከመሆኑም  ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት ጉልህ ሚና እንዳለው ነው ያስረዱት።

አገልግሎቱ "የሃገራችንን ኢኮኖሚ ማሳለጥ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎቻችንን በተሻለ ፈጣን በሆነ መልኩ መረጃን በመስጠትና በመቀበል ሂደት ትልቅ አቅም ያለው ማህበረሰብ ከመገንባት አኳያ ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ" እንደሆነ ነው ዋናሥራ አስፈፃሚዋ ያመለከቱት።

ብቁ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ማስፋፋታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።


የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስገን በበኩላቸው፤ በከተማዋ የአገልግሎቱ መጀመር ከግለሰብ እስከ ንግዱ ማህበረሰብ ቀልጣፋ አሰራርን በማሳለጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

ከንቲባው " የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ አገልግሎት መጀመሩ ሰዎች በቤታቸው ሆነው አለም የደረሰችበትን ሁኔታ በማየት ራሳቸውን ለለውጥ እንዲያዘጋጁ ያስችላቸዋል" ብለዋል።


የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ የነቀምቴ ዲስትሪክት ተወካይ አቶ ጉተማ ተርፋሳ በሰጡት አስተያየት፤  አገልግሎቱ በምዕራብ ሪጅን መጀመር በተለይም የፋይናንስ ተቋማትን ሥራ በማሳለጥ ሕብረተሰቡን በበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

"የ4ጂ.ኤል.ቲ.ኢ በነቀምቴ ከተማ አገልግሎት መጀመሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተማሪዎቻቸው ጋር በቀላሉ ለመገናኘት ያስችላቸዋል" ያሉት ደግሞ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ዲን አቶ ወንድሙ ቀኖ ናቸው።
በኩባንያው ይፋ የተደረገው የቴሌ ብር አገልግሎትም ለተማሪዎች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል ብለዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም እስካሁን ባደረጋቸው የአራተኛው ትውልድ የሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎት ማስፋፊያ ሥራዎች በምዕራቡ ሪጅንና አዲስ አበባን ጨምሮ 78 ከተሞችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም