በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሃይል ማመንጨትና ማስተላለፍ አበረታች ውጤት ተገኝቷል

253

አዳማ፣ መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሃይል ማመንጨትና ማስተላለፍ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ።

አሁን ሀገሪቷ ያላት 4ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም በቀጣይ 5 ዓመታት ወደ 12ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል ።

ከ800 በላይ የሚሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች የተሳተፉበት የ2013 ዓ.ም የስራ ክንውና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ገልማ አባገዳ እየተካሄደ ይገኛል።

ሚኒስትሩ በመድርኩ ላይ እንደገለፁት የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሀገሪቷን የተፈታተኑበት ወቅት የነበረ ቢሆንም ሃይል በማመንጨትና በማሰራጨት ጥሩ ውጤት መገኘቱን ገልፀዋል።

በቀጣይ አምስት ዓመታት አሁን ያለው 4ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ግብ በማስቀመጥ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብና ኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመነጫ ግድብ እንዲሁም አይሻና የአሰላ የነፋስ ሀይል ማመንጫን ጨምሮ ሌሎች አማራጭ ሃይል ማመንጫዎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በበጀት ዓመቱ 835 ሚሊዮን ዶላር ለሃይል ማስተላለፊየ መሰረተ ልማት ፈሰስ መደረጉን ጠቅሰው ለሃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታና አገልግሎት ተደራሽነት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር እየተመቻቸ መሆኑንም አመልክተዋል።

“ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የሀገሪቷ ህዝብ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያላገኘ በመሆኑ የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ ይገባናል" ብለዋል።

በቀጣይ 5 ዓመት "ብርሃን ለሁሉም" በሚል መርህ የሀገሪቷን ህዝብ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ይህን ለማሳካትም በዓመት 1 ሚሊዮን አባወራና እማወራ ተጠቃሚ ማድረግ አለብን ነው ያሉት። 

ዘርፉን ለማዘመን የሴክተሩ አጠቃላይ ሪፎርም፣ መዋቅራዊ አደረጃጀትና የታሪፍ ማሻሻያ ሪፎርም ተከናውኗል ብለዋል ።

የሀብት አጠቃቀምና የገበያ አስተዳደር በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት ።

“ዘመናዊ የሆነ የታዳሽ ሃይል በተለይ ከውሃ፣ ንፋስ፣ ከፀሃይና ከጂኦተርማል በማመንጨትና ተደራሽ ማድረግ የቀጣይ ቁልፍ ተግባራችን ነው" ብለዋል።

“እንቦጭን ማስወገድ የስንዴና ሌሎች ሰብሎች የመስኖ ልማት በአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች ናቸው” ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ለዚህም ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት ከኛ ይጠበቃል” ብለዋል።

“አሁን ሀገሪቷን የገጠማትን ችግር ሳንታክት በመፋለም ከዘላለም ባርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መላቀቅ አለብን” ብለዋል ። 

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት በዘርፉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግ፣ ብልሹ አሰራርን ለማስቀረትና የተሻለ አገልግሎት ለህዝቡ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር አመርቂ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል ።

ተቋሙ የስራ ክንውንና የተገኘው ውጤት በተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ግምገማዊ መድረኩ ማስፈለጉንም አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም