የቆቦ ጊራና ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በአሸባሪው ህወሃት ዝርፊያና ውድመት ደረሰበት

76

ጎንደር፡ መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ጊራና ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በህወሓት የሽብር ቡድን ዝርፊያና ውድመት እንደደረሰበት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የደረሰውን ውድመት ተከትሎ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ስራ በማቆሙ ከ8ሺህ በላይ በመስኖ ልማቱ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተፈናቅለው ከምርት ስራ ውጭ ሆነዋል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አበባው ጌቴ ለኢዜአ እንደገለጹት የህወሓት የሽብር ቡድን በሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ሲፈጽም እንደቆየው ሁሉ የህዝብ መጠቀሚያ በሆነው የመስኖ አውታር ላይም ዝርፊያና ውድመት መፈፀሙን መረጃው ደርሶናል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩን ለችግር ማጋለጡን እንደቀጠለ መሆኑን ገልጸው የመስኖ ፕሮጀክቱ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳትም ሙሉ በሙሉ ስራ ማቆሙንና ከ8 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ከምርት ስራ ውጭ እንደሆኑም ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከ2ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የሚያለሙበት ዘመናዊ የመስኖ አውታር እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮች በመስኖ ልማቱ አትክልትና ፍራፍሬ በስፋት አምርተው ለገበያ በማቅረብና እራሳቸውም በመጠቀም የምግብ ዋስትናቸውን ያረጋገጡበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር አቶ አበባው ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በመስኖ አውታሩ ላይ በፈፀመው ውድመትና ዝርፊያ መስኖ አልሚ አርሶ አደሮች ከመስኖ ስራቸው ተፈናቅለው ለተረጂነት መጋለጣቸውን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ በበኩላቸው የህወሃት የሽብር ቡድን ወደ ክልሉ ዘልቆ በመግባት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የአርሶ አደሮች የግብርና ስራ መስተጓጎሉንና በለማ ሰብል ላይም ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

ወራሪው ሃይል ተደምስሶ በወጣባቸው አካባቢዎች በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ ያደረሰውን የጉዳት መጠን በመለየት የመልሶ ማቋቋም ስራ ለመጀመር በክልሉ መንግስትና በግብርና ቢሮው ደረጃ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንም አስታውቀዋል።

“የሰብል ጉዳት የደረሰባቸውን አርሶ አደሮች በቀሪ እርጠበትና በመስኖ ልማት በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ መልሶ የማቋቋም ስራዎች በትኩረት ይሰራሉ” ብለዋል።

“ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ለማቅረብ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ አካባቢዎቹ ሙሉ በሙሉ ከወራሪው ነጻ መሆን ሲጀምሩ አርሶ አደሮቹን የማቋቋም ስራዎቹ በፍጥነት ይጀመራሉ” ብለዋል።

የቆቦ ጊራና የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በረጅም ጊዜ እቅድ እስከ 70 ሺህ ሄክታር በማልማት የአካባቢውን አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በክልሉ መንግስት የተገነባ ፕሮጀክት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም