ክልሎች በቤት ግንባታ ለሚሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማት ብድር እንዲመቻች ጠየቁ

47

መስከረም 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ክልሎች በቤት ግንባታ ለሚሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማት ብድር እንዲመቻች እና ከግንባታ አቅርቦት ጋር ያሉ ችግሮችም እንዲፈቱ ጠየቁ።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በበኩሉ ክልሎች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሰራሁ ነው ብሏል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም በጀት የእቅድ አፈጻጸምና የ2014  በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል።።

የክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊዎች በቤት ግንባታ ለሚሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማት ብድር እንዲመቻች እና ከግንባታ አቅርቦት ጋር ያሉ ችግሮችም እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

የፌደራል መንግሥት ለቤቶች ግንባታ መፋጠን በተለያየ መልኩ ተደራጅተው ግንባታ ለሚያከናውኑ ግለሰቦችና ተቋማት የብድር አቅርቦት የሚያገኙበት  አሰራር መዘርጋት አለበት ብለዋል።

የብድር አቅርቦቱ ከተመቻቸ  የቤቶች ግንባታን ማፋጠን ይቻላል ያሉ ሲሆን፤ ዜጎች በዘላቂነት የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት ነው ያሉት።

ለቤቶች ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብአቶች በሚፈለገው መልኩ አለመሟላት ግንባታዎችን እያዘገየ መሆኑንና  አስቸኳይ መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ለቤቶች ግንባታ የሚያስፈልግ መሬት ለማቅረብ ከይዞታቸው ለሚነሱ ዜጎች የሚከፈል የካሳ ክፍያ ክልሎች በሚፈለገው ፍጥነት እንደማይፈጽሙና ይህም ክፍያቸውን በበጀታቸው ውስጥ ያለማካተትና የገቢ ግብር በበቂ ሁኔታ አለመሰብሰብ ችግር እንደሆነ አንስተዋል።

የተጠቀሱትን ችግሮች በመፍታት የካሳ ክፍያ በወቅቱ በመፈጸም የግንባታ ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ የክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊዎች አመልክተዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የእቅድ ፖሊሲና ፕሮግራም በጀት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጃው ባይጨክን በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የቤቶች ልማት ዘርፍ አፈጻጸም ብዙ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው ያመላከተ እንደሆነ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ማህበራት 76 ሺህ 125 ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ 79 ሺህ 21 ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፤ በግለሰቦች 32 ሺህ 625 ቤቶች ለመገንባት ታስቦ 256 ሺህ 976 ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

ይሁንና በመንግሥት 6 ሺህ 538 ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ 5 ሺህ 499 ቤቶች መገንባታቸውንና በገጠር ማዕከላት 37 ሺህ ቤት ለመገንባት ታስቦ ማጠናቀቅ የታቻለው 12 ሺህ 210 ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል።

በሪል ስቴት 21 ሺህ 750 ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ የተገነባው 3 ሺህ 994 ብቻ ነው።

የወሰን ማስከበር፣ የካሳ ክፍያና የመሬት አቅርቦት ችግር ለቤቶች ግንባታ አፈጻጸም የሚፈለገውን ያህል አለመሆን አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል አቶ ደረጃው።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልሎቹ ጋር በተቀናጀ መልኩ በመስራት ለችግሮቹ መፍትሔ ለማበጀት በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በ2014  በጀት ዓመት በዘርፉ ያለውን አፈጻጸም ለማሻሻል ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያዘጋጀው የውይይት እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን በመድረኩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም