የሞጆ - መቂ - ባቱ የፍጥነት መንገድ የኢትዮጵያን የወጪ ገቢ ንግድ አማራጭ ያሰፋል

178

መስከረም 10/2014 (ኢዜአ)  የሞጆ - መቂ - ባቱ የፍጥነት መንገድ የኢትዮጵያን የወጪ ገቢ ንግድ አማራጭ የሚያሰፋ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የሞጆ - መቂ - ባቱ የምዕራፍ አንድ የክፍያ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ባለፈው ሚያዚያ ወር በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ መመረቁ ይታወሳል።

የክፍያ የፍጥነት መንገዱ ከዛሬ ጀምሮ ለተሽከርካሪዎች ያልተቋረጠ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት ክፍት የተደረገ ሲሆን መንገዱ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስመልክቶ ይፋዊ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለልጣን፣ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል፤ መንገዱ ከአዲስ አበባ - አዳማ እና ድሬደዋ - ደወሌ የክፍያ መንገዶች በመቀጠል ሶስተኛው የክፍያ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

የክፍያ መንገዶች ለህብረተሰቡ ምቹ አገልግሎት የሚሰጡ ከመሆናቸው ባሻገር ለዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በዚህም እስካሁን 1 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንዲሁም ለ300 ሰዎች ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

በክፍያ መንገዶች እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ተስተናግደው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፤ የክፍያ መንገዱ ለኢትዮጵያ ተስፋ የሚሰጥና ማህበረሰቡም ዘመናዊ፣ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

መንገዱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ጭምር ያለውን የክፍያ መንገዶች ቁጥር በማሳደግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ፤ የክፍያ መንገዱ ዘመናዊ እና ለአገልግሎት አመቺ ሆኖ መገንባቱን ገልጸዋል።

መንገዱ የጉዞ ሰዓትን በመቀነስ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

መንገዱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ለምታደርገው የንግድ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ብሎም የወጪ ገቢ ንግድ አማራጯን የሚያሰፋ ነው ብለዋል።   

የክፍያ መንገዱ 92 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 32 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን 5 ደረጃቸውን የጠበቁ የክፍያ ጣቢያዎችም አሉት። 

የክፍያ ጣቢያዎቹም ሞጆ፣ ቦቴ፣ ቆቃ፣ መቂ እና ባቱ መውጫ ጣቢያዎች መሆናቸው ታውቋል።

የክፍያ መንገዱ በአጠቃላይ በ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ውጪ የተገነባ ሲሆን፤ ግንባታውም ከኮሪያ ኤግዚም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር እና በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈ ነው።

የክፍያ መንገዱ የአዲስ አበባ አዳማ ሞያሌ- ሞምባሳ የመንገድ ኮሪደር አካል ሲሆን፤ በአፍሪካ የክፍያ መንገድ የሚገኙ አገራትን በማገናኘት ከግብጽ-ካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን 10 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እንደሆነ ተገልጿል። 

የምዕራፍ ሁለት የባቱ - አርሲነገሌ- ሐዋሳ የመንገድ ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም