ተመራቂዎች በሀገሪቱ የህልውና ማስጠበቅ ዘመቻ ላይ በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

73

ደብረብርሀን፤ መስከረም 9/ 2014( ኢዜአ) ተመራቂዎች በአሁኑ ወቅት ሀገር ለማዳን እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ ላይ በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

የደብረ ብርሃን መምህራን ኮሌጅ በክረምት መርሀ ግብር ያሰለጠናቸው  1ሺህ 73 መምህራን ዛሬ በዲፕሎማ አስመርቋል፤ ከመካከላቸውም  770 ሰዎች  ኮሌጁ ከአዲስ  አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸው የቅድመ መደበኛ መምህራን ይገኙበታል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት የተገኙት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ  ምክትል  ሀላፊ አቶ ዳኘው ገብሩ፤ እንዳሉት ተመራቂ መምህራን  በሀገሪቱን  የህልውና  ማስጠበቅ ዘመቻ ላይ  መሳተፍ አለባቸው።

የህልውና ዘመቻው ግንባር ብቻ በመሰለፍ ሳይሆን በደጀንነትና በተሰማሩበት ሙያ ከተለመደው የላቀ አገልግሎት መስጠት በመቻል መሆኑን አመላክተዋል።

የዛሬ ተመራቂ መምህራን ስነ-ምግባርን በመላበስ ህጻናትን በእውቀትና በግብረ ገብነት ኮትኩተው በማሳደግ ምስጉን ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የሀገሪቱን እድገት ለማፋጠን የሚያስችል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ መምህራንን ለማስተማር አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በቅድመ መደበኛ የሚያስተምሩ መምህራንን ከደብረ ብርሃን መምህራን ኮሌጅ ጋር በመተባበር ማሰልጠኑ ለሰው ሃይል ግንባታ ካለው ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን መምህራን ኮሌጅ ዲን ወይዘሮ ታለፍ ፍታወቅ በበኩላቸው፤ የዛሬ ተመራቂዎችም በተማሩበት ሙያ ህጻናትን በስነ ምግባር በማነጽ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት መሰረት ማስያዝ አለባቸው ብዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከልም 770 ሰዎች  ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር የስራ ላይ ስልጠና የወሰዱና ቀሪዎቹ ደግሞ ከክልሉ የተወጣጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 ከአጠቃላይ  ተመራቂዎች መካከልም 740  ሴቶች ናቸው ።

ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ  የሆነችው  መዓዛድንግል ሰይፈ በሰጠችው አስተያየት፤  የህልውና ዘመቻውን በገንዘብና በቁሳቁስ ከመደገፍ በሻገር በሙያዋ ብቁ ዜጋ ለማፍራት እንደምትጥር ተናግራለች።

ለዚህም ከወላጆች የምንረከባቸውን ህፃናት ተንከባክቦ በመያዝና በማስተማር  የመጠበቅ  ሃላፊነትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ነው ያስታወቀችው ።

ሌላው የዋንጫው ተሸላሚ አደግ ወልደሀና በበኩሉ፤ ተማሪዎችን ከማስተማር ጎን ለጎን አካባቢውን ነቅቶ ከአሸባሪው የህወሃት ተላላኪዎች ለመጠበቅ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም