ምርጫው ተዓማኒ፣ ፍትሃዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው-የብልፅግና ፓርቲ እጩዎች

73

አዲስ አበባ መስከረም 9/2014 (ኢዜአ) ምርጫው ተዓማኒ፣ ፍትሃዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ እጩዎች ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ጽህፈት ቤት የምረጡኝ ቅስቀሳውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳዳር ኡድሪን በድሪን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።

የምርጫ ቦርድ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አከባቢዎች ሁለተኛ ዙር ምርጫ ለማካሄድ በያዘው ቀጠሮ መሠረት በሐረሪ ክልል መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ምርጫ የሚካሄድ ይሆናል።

በዚህም የሐረሪ ብልጽግና ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች ምርጫው ተዓማኒ፣ ፍትሃዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል። 

የፓርቲው እጩ ተወዳዳሪ ወይዘሮ አሚን አብዱልከሪም እንዳሉት በሐረሪ ክልል የሚካሄደው ምርጫ በሰላማዊና ፍትሃዊ መልኩ እንዲከናወን እየተሰራ ነው።

እርሳቸው በምርጫው ካሸነፉ ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ብቁ ሆነው እንዲወጡና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሴቶች ያላቸውን እምቅ አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙና እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌለኛው የፓርቲው እጩ ተወዳደሪ ወጣት ሃምዲ ሳልሃዲን፤ በክልሉ ወጣቶች በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ፓርቲያቸው ብልጽግና ወጣቱ በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ መሆኑንም ነው ያስረዳችው።

የብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አብዱልሃኪም ኡመር፤ ምርጫው ከክልሉ በተጫማሪ የክልሉ ተወላጆች በሚገኙባቸው አጎራባች ክልሎችም የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋ፣ በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል በተመረጡ ቦታዎች የሚካሄድ መሆኑንም ጠቁመው ለዚህም ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በምርጫ ቅስቀሳው ላይ የተገኙ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ደም ለግሰዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም