የተዘረፉባቸው ና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ንብረቶቻቸው እንዲመለሱላቸው የጅግጅጋ ነዋሪዎች ጠየቁ

101
ጅግጅጋ ነሀሴ 9/2010 በሶማሌ ክልል ሁከት ተከስቶ በነበረበት ጊዜ የተዘረፉባቸውና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ንብረቶቻቸው ቶሎ ስላልተመለሱላቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ቅሬታቸውን ለኢዜአ ያቀረቡ የጅግጅጋ ነዋሪዎች ተናገሩ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ የተዘረፉትን ንብረቶች ለባለቤቶቹ መመለስ እንዲቻል ኮሚቴ ማቋቋሙንና ተገቢው ማጣራት ከተደረገ በኋላ ንብረቶቹ እንደሚመለሱ አስታውቋል። በሶማሌ ክልል መዲና ጅግጅጋና በሌሎች የክልሉ ከተሞች ተከስቶ በነበረው ሁከት በርካታ ንብረት ተዘርፏል። በተለይም በጅግጅጋ ከተማ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ባጃጅን ጨምሮ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ተዘርፈው ከከተማዋ የወጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም ፖሊሰ የተወሰኑትን ማስመለሱን በስፍራው የሚገኘው የኢዜአ ጋዜጠኞች ቡድን ተመልክቷል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ግን የተመለሱት ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች በትክክል የሚታወቁ ሆኖ ሳለ ፖሊስ ለባለንብረቶቹ በፍጥነት መመለስ አልቻለም። "በመሆኑም ችግር ውስጥ ወድቀናል" ሲሉ ነው የተሽከርካሪዎች ባለቤቶች ነን የሚሉት አካላት ቅሬታቸውን የገለፁት። ጉዳዩን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ፍርሃን ዳሂር ፖሊስ የተዘረፉ ንብረቶችን ማስመለስ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ያም ሆኖ ከተዘረፉት ንብረቶች ብዛት አንጻር ፖሊስ ብቻውን በሚገባው ፍጥነት መሄድ አለመቻሉን ጠቅሰው ፈጣን ምላሽ መስጠት ይቻል ዘንድ ከሁሉም ከህብረተሰቡ የተውጣጣ ንብረት አስመላሽ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልፀዋል። "ኮሚቴው ተገቢውን ማጣራት ካደረገ በኋላ በፖሊስ በኩል በእስካሁን ሂደት የተያዙ ንብረቶች ለባለቤቶቻቸው እንዲመለሱ ይደረጋል" ብለዋል ኮሚሽነሩ። የአስመላሽ ኮሚቴው ፀሃፊ አቶ ጉሌድ አውአሊ በበኩላቸው ኮሚቴው የተዘረፉ ንብረቶችን በፍጥነት በማሰባሰብ ለባለቤቶቹ መመለስ እንዲቻል ከእስልምና እምነት አባቶች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አውስተዋል። የሃይማኖቱ አባቶች በቀን አምስት ጊዜ በየመስጂዱ በሚከወኑ ስርዓተ ፀሎቶች (ሰላት) ላይ ህዝቡ ከተለያዩ አካባቢዎች የተዘረፉ ንብረቶችን በማስመለስ ለፖሊስ እንዲያስረክብ እያስተማሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። ኮሚቴው ሊብሬዎችን ጨምሮ ሌሎች ተገቢ መረጃዎችን በማመሳከር በተቻለው ፍጥነት በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን ለባለንብረቶች ለመመለስ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል። በሶማሌ ክልል አንዳንድ ከተሞች ከ13 ቀናት በፊት ተከስቶ በነበረው ሁከት በተለይ ጅግጅጋ የወትሮ ድምቀቷ ተለይቷት የከረመች ቢሆንም ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ የቀድሞ ሰላሟ እየተመለሰ ነው። በክልሉ ተከስቶ በነበረው ሁከት በርካታ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ የንግድ ቤቶችም ተዘርፈዋል፤ በዚህም ሳቢያ በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ህዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለመጠለል ተገዷል። ዛሬ በክልሉ ተከስቶ በነበረው ሁከት ላይ የሚመክር ህዝባዊ ጉባዔ በጅግጅጋ ከተማ ይካሄዳል። ተወያዮቹ በሁከቱ የተዘረፉ ንብረቶችን ማስመለስና አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ይመክራሉ ተብሏል። ኢዜአ ከከተማ መስተዳደሩ ባገኘው መረጃ መሰረት ጉባዔው በየቀበሌዎች የሚካሄድ ሲሆን በርካታ ህዝብ ይሳተፍበታል ተብሎም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም