በአዳማ ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ጠፋ

67
አዳማ ነሃሴ 9/2010 በአዳማ ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ። የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሳጅን ወርቅነሽ ገልሜቻ እንድገለጹት አደጋው የደረሰው ትናንት ምሽት እንድ ሰዓት ላይ በአባ ገዳ ክፍለ ከተማ ኦዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቀጠና ሰባት በሚባል ቦታ ነው። የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3/32107 ኦሮ የሆነ አይሱዙ ባደረሰው አደጋ ማታ ለመዝናናት ከቤታቸው ወጥተው በእግር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሦስት  ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል። የሁለትና የአምስት ዓመት ህፃናትን ጨምሮ የ25 ዓመት ወጣት ህይወታቸውን ሲያጡ አንድ የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድርሱንም ጨምረው ገልጸዋል። አደጋው ሊደርስ የቻለው የአሽከርካሪው ረዳት በሰፈር ውስጥ እየተዘዋወረ ከሰል ለማከፋፈል ሲሞክር መሆኑንም አስረድተዋል። በወቅቱ አደጋውን አድርሶ ለጊዜው የተሰወረውን ረዳት ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጽው የመኪናው ሾፌር በቁጥጥር ሥር ውሎ ፖሊስ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በምሽትም ሆነ በቀን በችለተኝነት ከቤት እንዲወጡ ማድረግ የለባቸውም ያሉት ሳጅን ወርቅነሽ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ሁሉም ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም