አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ላይ የሚያቀርቡትን የተዛባ ዘገባ በእውነተኛ መረጃ መመከት ያስፈልጋል

89

መስከረም 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ላይ የሚያቀርቡትን የተዛባ ዘገባ በእውነተኛ መረጃ መመከት እንደሚያስፈልግ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያውያን አመለከተ።  

የመገናኛ ብዙሀኑ ከአሸባሪው ህወሓት የተዛባ መረጃ በመውሰድ የሚያቀርቡትን የተሳሳተ ዘገባ በእውነተኛ መረጃ መመከት እንደሚገባ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የጥምረቱ አባላት ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት ሆስፒታሎችን፣ የእምነት ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን ማውደሙ እንዲሁም ህጻናት በጦርነት እንዲሳተፉ ማድረጉ የዓለም አቀፍ ህግን በሚጻረር እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በተቃራኒው ቡድኑ ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የሀሰት መረጃ እየሰጠ ትክክልኛ ያልሆነና የተዛባ መረጃ እያሰራጩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በዚህም "በነጩ ፖስታ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ያለውን እውነት ለማሳወቅ እየተንቀሳቀስን ነው" ብለዋል የጥምረቱ አባላት።

አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ስለኢትዮጵያ በሚያቀርቡት የሀሰት ዜና የምዕራቡ ዓለም ማህበረሰብ የተዛባ አቋም እንዲይዙ ማድረጉን አትተዋል።

መገናኛ ብዙሃን የሀሰት መረጃ በመያዝና በመጠቀም "በኢትዮጵያ ላይ ጥሩ ያልሆነ ዘመቻ እያደረጉ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና ሊያቆሙ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የዩዝ ኢምፓወርመንት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ሰይፉ "አሸባሪው ህወሓት እያራመደው ያለው ነገር ውሸትን ማዕከል ያደረገ ነው" ብለዋል።

በዚህም የተዛባ መረጃ እየተሰራጨና የተሳሳተ አቋም እየተያዘ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉሱ ለገሰ በበኩላቸው የሚዲያዎቹ የተሳሳተ ዘገባ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ምዕራባውያን እንዳይረዱ ማድረጉን ተናግረዋል።

የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር "ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም ልዩነት ለአገሩ አንድነት መቆም አለበት" ብለዋል።

አገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ የውስጥም ሆነ ውጭ አገራትን በጋራ ማስቆም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ማንኛውም ሰው አገርና ሰላም ከሌለ መኖር ስለማይችል ለአገሩ የቻለውን ሁሉ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስከላ ለማ ትውልዱ የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕትነት መክፈል እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም