በአንድ እጃችን ትጥቅ በአንድ እጃችን ደግሞ ማረሻችንን ይዘን የግብርና ስራችንን አሳክተናል

97

ጎንደር መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) በአንድ እጃችን ትጥቅ በአንድ እጃችን ደግሞ ማረሻችንን ይዘን ወራሪውን በመመከቱ ተግባር በመሳተፍ የግብርና ስራችንን አሳክተናል ሲሉ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ በእርሻ ስራ የተሰማሩ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

ዞን አቀፍ የአኩሪ አተር የኩታ ገጠም የእርሻ ቴክኖሎጂ ልማት የመስክ ጉብኝት በጠገዴ ወረዳ ማርዘነብ ቀበሌ ተካሂዷል፡፡

በወረዳው በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ዛይድ ወርቄ፤  የህወሃት የሽብር ቡድኑ የእርሻ ኢንቨስትመንቱን ለማደናቀፍ በአካባቢው የወረራ ሙከራ ቢያደርግም መክተን መመለስ ችለናል ብለዋል።

ከሰራዊቱ ጋር በመሆን ወራሪውን ቡድን በጀግንነት በመመከትም በመኸር ወቅቱ 42 ሄክታር አኩሪ አተር ለማልማት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

ካለሙት አኩሪ አተር እስከ አንድ ሺህ 260 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ጠቅሰው፤ ምርቱን ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ የውል ስምምነት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ የአካባቢውን የእርሻ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም ያሉት ደግሞ ሌላው ባለሀብት  አቶ አበበ ንጉሴ ናቸው።

''በአንድ እጄ ትጥቄን በአንድ እጄ ደግሞ ትራክተር ተከራይቼ በማረስ 60 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር መሸፈን ችያለሁ፤ ካለማሁት መሬትም እስከ 1ሺ 800 ኩንታል ምርት እጠብቃለሁ ነው ያሉት።

በወረዳው የማርዘነብ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል አላምረው ንጉሴ በበኩላቸው፤ ወራሪው የሽብር ቡድን የእርሻ ስራዬን ያደናቅፍብኛል በሚል ስጋት ትጥቄንና ማረሻዬን አንድ ላይ በማቀናጀት 12 ሄክታር አኩሪ አተር ማልማት ችያለሁ ብለዋል።

በኩታ ገጠም እርሻ 15 ሄክታር አኩሪ አተር ማልማታቸውን ገልጸው የሚጠብቁትን 450 ኩንታል ምርት ውል ገብተው ለአግሮ ኢንዱስትሪ ማቀናበሪያ ለማስረከብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በወረዳው በጥቅምት ወር ሰብል እንዳይሰበሰብ፤ በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ደግሞ የእርሻ ኢንቨስትመንት ስራው እንዳይጀመር የከፈተውን ጦርነትና ወረራ ማክሸፍ ተችሏል ያሉት የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዘውዴ ጀጃው ናቸው፡፤

በ2013/14 የመኸር ወቅት 72 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዘር በመሸፈን የወረዳውን የግብርና ስራ ማሳካት መቻሉን ያመለከቱት ሃላፊው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም 4 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ አኩሪ አተር በባለሀብቶችና በአርሶ አደሮች መልማቱን ጠቁመው፤ 120 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብ ነው ያመለከቱት፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ነጋ ይስማው በበኩላቸው፤ ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን የግብርና ልማት እቅዶችን ለማሳከት በተደረገው ርብርብ 480 ሺ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን እቅዱን ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡

በምርት ዘመኑ በተለይ አኩሪ አተርን በኩታ ገጠም እርሻ ለማልማት በተደረገው ርብርብ 16ሺ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ጠቁመው፤ ከለማው ሰብል ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ መታቀዱን  ተናግረዋል፡፡

በመስክ ጉብኝቱ ፤  አርሶ አደሮችና የእርሻ ባለሀብቶች፣ የክልል ግብርና ቢሮ አመራሮች፣ የግብርና ምርምር ማእከላት ተመራማሪዎችና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ የስራ ሃላፊዎች መገኘታቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም