በኢሉአባቦር ዞን የቡና ልማት የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ ነው

92
መቱ ነሀሴ 8/2010  ምርጥ የቡና ችግኝ በመትከል የቡና ልማትን የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የኢሉ አባቦር ንኑ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን ገለጸ፡፡ እስካሁንም ቀደም ብለው የተዘጋጁ ከ118 ሚሊዮን በላይ  ምርጥ የቡና ችግኝ በተያዘው የክረምት ወቅት ተተክሎ እንክብካቤ እየተደረገለት ይገኛል፡፡ የባለስልጣኑ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ንጉሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት የቡና ችግኙ የተተለው ከ35 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ነው፡፡ ለቡና ችግኞቹ በልማቱ የተሳተፉ ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንክብካቤ እያደረጉ ሲሆን  አብዛኛዎቹ ዝርያዎች ከጅማ ግብርና ምርምር የተገኘ ምርጥ ዝርያ ናቸው። አርሶአደሩ ቀደም ሲል ለረጅም ዓመታት ሲያለማ የነበረው የቡና ዝርያ ምርታማነት በሄክታር ከስድስት ኩንታል እንደማይበልጥ የተናገሩት አቶ አዲሱ የተሻሻለው ዝርያ በአግባቡ ከተያዘ  እስከ 20 ኩንታል ምርት መስጠት አንደሚችል ገልጸዋል፡፡ "ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰብስበው በጅማ ግብርና ምርምር የተዳቀሉ እና ከኢሉአባቦር ጫካዎች የተሰበሰቡ  ዝርያዎችን ለአርሶአደር እየተሰራጨ ይገኛል" ብለዋል። የቡና ልማቱ የመስፋፈቱ ስራ አሁንም ቀጥሎ እንዳለና ይህም ልማቱን በማፋጠን ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው ዓመታዊ  የቡና ምርት መጠን ለማሳደግ ያስችላል፡፡ አርሶ አደር አለማየሁ ሽፈራው በዞኑ አሌ ወረዳ የገርበዲማ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከአስር ሄክታር  ደን ጋር ቡናን በጥምር  እያለሙ ነው። አርሶ አደሩ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ወራትም ከአንድ ሺህ በላይ ምርጥ የቡና ችግኝ ተክለው እየተንከባከቡ ይገኛሉ፡፡ በመቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ በቡና ልማት የተሰማሩት አርሶ አደር  ደጋጋ ፊጤ በበኩላቸው በቀበሌያቸው ከሚገኙ ሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በቡድን በመሆን የተከሏቸውን ችግኞች ከሰውና እንስሳት ንክኪ ከልለው እየተንከባከቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኢሉአባቦር ዞን እስካሁን ከ250 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ሲሆን በየዓመቱም እስከ 60 ሺህ ቶን ምርት ይሰበሰባል። ከሚሰበሰበው ምርት ውስጥ 23 ሺ ቶን የሚሆነው ደግሞ ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም