"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" የትዊተር ዘመቻና የማህደር ምስል ዛሬ ይቀየራል

124

አዲስ አበባ፤መስከረም 7/2014(ኢዜአ) "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" የትዊተር ዘመቻና የማህደር ምስል ዛሬ ከቀኑ 7፡00 ሠዓት ከ7 ደቂቃ ላይ የመቀየር መርሃ ግብር እንደሚካሄድ የዘመቻው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ።

የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊያን በተጠቀሰው ሠዓት የማህደር ምስላቸውን /ፕሮፋይል ፒክቸር/ የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት በሚል በተዘጋጀው እንዲቀይሩም ጥሪ ቀርቧል።

ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ ማስረዳትና የህወሓት ቡድን እየፈጸማቸው ያሉ እኩይ ተግባራትን ማጋለጥን ዓላማ ያደረገው "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም ነው የተጀመረው።

በዘመቻው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉበትም ይገኛሉ።

የዚሁ ዘመቻ አካል የሆነው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች የማህደር ምስላቸውን /ፕሮፋይል ፒክቸር/ ነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት በሚል በተዘጋጀው ፕሮፋይል ፎቶ የሚቀይሩበት መርሃ ግብር ዛሬ እንደሚካሄድ የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ ታደሰ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የማህደር ምስል የሚቀየርበት መርሃ ግብር ከቀኑ 7፡00 ሠዓት ከ7 ደቂቃ ላይ የሚካሄድ ሲሆን በዚሁ ሠዓት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ምስሉን መቀየር አለበት ብለዋል።

በተጨማሪም የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት ዘመቻ ዓላማዎችን መሰረት ያደረገ የትዊተር ዘመቻ እንደሚካሄድና ለዘመቻው የሚሆኑ አቢይ ርዕሶች /ሀሽታጎች/ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ዜጎች በተዘጋጁት መርሃ ግብሮች በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ወገንተኝነት እንዲያሳዩ አቶ አክሊሉ ጥሪ አቅርበዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" የተጻፉ ደብዳቤዎች የፖስታና የተለያዩ እቃዎችን በዲኤችኤል አማካኝነት ወደ ዋይት ሐውስ እንደሚላኩ ጠቁመዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

መርሃ ግብሩን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ዩዝ ኢምፓወርመንት ማኅበርና አገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም