በኮሮና መከላከልና ህክምና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎች ዕውቅና ተሰጠ

195

ሐዋሳ መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በኮሮና መከላከልና ህክምና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎችና የእንክብካቤ ሰራተኞች ምስጋናና ዕውቅና ሰጠ።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙንጣሻ አብርሃም በወቅቱ እንዳሉት የጤና ባለሙያዎች ኮሮናን ለመከላከል ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ጉዳቱ የከፋ እንዳይሆን አስችሏል።

“ቫይረሱ ሲከሰት በተቋምም ሆነ በባለሙያ ደረጃ ምንም ዝግጅት ያልነበረበት ቢሆንም መንግስት ያደረገውን ጥሪ በመቀበል ህይወታችሁን ሰጥታችሁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከታችሁ ባለሙያዎች ጀግኖች ናችሁና ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች” ብለዋል።

የሌሎችን ህይወት ለማዳን ባደረጉት ጥረት ራሳቸው በቫይረሱ ተይዘው ህይወታቸውን ያጡ የጤና ባለሙያዎች መኖራቸውን ጠቁመው ለባለሞያዎቹና ሌሎች ባለድርሻ አካለት የምስጋና ምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት መበርከቱን አስታውቀዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ካንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በበኩላቸው ባልተመቻቸና የህክምና ግብአት ባልተሟላበት ሁኔታ ህይወት ለማዳን ርብርብ ላደረጉ የጤና ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶችና ተቋማት ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባው አክለው ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተሻለ የህክምናና ምርመራ ለማግኘት ወደ ሐዋሳ በሚመጣው ህዝብ የሚፈጠር ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ህይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት ለወገን ሀሌታ የሆኑ የጤና ባለሙያዎች  ተግባር የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል።

“ለወገን መስዋእት መሆንና ከራስ ይልቅ ለሌላው ማሰብ ኢትዮጵያዊነት ነው” ያሉት ምክትል ካንቲባው ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቫይረሱን በመከላከል ረገድ የሚያኮራ ተጋድሎ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ቫይረሱ በተከሰተ ጊዜ ከፍተኛ ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው የተናገሩት በሐዋሳ ዩኒቨረሲቲ ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ መሀመድ አደም በበኩላቸው በወቅቱ ሙያዊ ግዴታቸው በመሆኑ ስራውን በአግባቡ ለመወጣት ወስነው ሀላፊነታቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል ።

በስራ ሂደት ከባድ ፈተና ሲገጥማቸው የነበረ ቢሆንም ያንን በሟቋም ዛሬ ላይ ለመመሰጋገን በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል::

በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ መከላከል አማካሪ ግብረ ሃይል አባልና የያኔት ሆስፒታል ባለቤት ዶክተር ግርማ አባቢ ቫይረሱን በመከላከል ሂደት የጤና ተቋማትና ግለሰቦችን በማስተባበር ረገድ አስተዳደሩ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

“ቫይረሱ ያልጠፋ በመሆኑ ወደፊትም የሚገጥመውን ችግር በጋራ ለመቋቋም ዕውቅናው ተጨማሪ አቅም ይሆናል” ብለዋል።

በሀዋሳ ከተማ የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል የጤና ባለሙያ ሂሩት ሳህሌ በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎች ላደረጉት ተጋድሎ የምስጋና ስነ ስርአት መዘጋጀቱ በቀጣይ በበለጠ  ለመስራት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።