የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የባህል፣ ጥናትና ምርምር ማእከል ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራረመ

65

አምቦ ፤መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የባህል፣ ጥናትና ምርምር ማእከል ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

ማእከሉና ሚኒስቴሩ ዛሬ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ  ስምምነቱን ተፈራርመዋል ።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብዙነሽ ሚደቅሳና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት ስምምነቱን ፈርመዋል።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የባህል፣ ጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሌይኩን በወቅቱ እንደገለጹት ስምምነቱ የተፈረመው በአርት፣ በኪነ-ጥበብ፣ በቋንቋ ልማት እንዲሁም በሀገር በቀል እውቀት ዘርፎች በትብብር ለመስራት ነው ።

ስምምነቱ በእውቀት ዘርፎቹ በመማር ማስተማርና በጥናትና ምርምር በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።

ማእከሉ በሚሰራቸው ስራዎች እስካሁን ከአራት ተቋማት ጋር የትብብር ስምምነት በመፈረም ድጋፍ እያገኘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኮሪያ የኮይካ ድርጅት 32 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳ "ስምምነቱ በታላቁ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የባህል ማእከል  በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ታሪክ ላይ ሃሳብ እንድንለዋወጥና የስራ ግንኙነት እንድንፈጥር ያደርጋል" ብለዋል፡፡

የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የባህል፣ ጥናትና ምርምር ማእከል በስነ ጽሁፍ ውስጥ ያለፍን ብቻ ሳንሆን በኢትዮጵያ ውስጥ አንባቢ የነበረ ሁሉ በጸጋዬ ገብረመድህን ስራ የተቀረጹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“ጸጋዬ ገብረመድህን የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ዜጋ ሆኖ እንዲቀጥል በስነ ጽሁፍ አማካነት አስተሳሰብን በመቅረጽ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው” ብለዋል፡፡

በተለይ የስነ ጽሁፍ እድገት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ትልቅ መሰረት የጣሉ የስነጽሁፍ ሊቅ መሆናቸውን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

በስምምነት ፊርማ ስነ ስርአቱ ላይ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም