የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

105
አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2010 የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር ተወያዩ። ዶክተር  ወርቅነህ ዛሬ በጂቡቲ ከፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያና ጂቡቲ መካከል ያለው ግንኙነት በሁኔታዎችና በአጋጣሚ የማይለወጥ መሆኑን አስምረውበታል። የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ስትራቴጂካዊ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በጂቡቲ የሚኖሩ የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን በጸጥታ ስጋት ምክንያት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ያነሱት ዶክተር ወርቅነህ  ኢትዮጵያዊያን ጂቡቲን ሁለተኛ አገራቸው አድርገው የሚቆጥሩ በመሆኑ ያለ ስጋት እንዲኖሩ የጂቡቲ መንግስት አስፈላጊውን እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ፕሬዝዳንት ኢስማኢል ኦማር ጊሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን በጂቡቲ ውስጥ ያለ ምንም ችግር መኖር እንደሚችሉና መንግስታቸውም ይህን ለማድረግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላት፤ ለዚህም ዕውን መሆን እንደወትሮው ሁሉ አሁንም እንደምትሰራ ተናግረዋል። ሁለቱ ሕዝቦች በደምና በታሪክ ተሳስረው አብረው የሚኖሩ በመሆናቸው ይህ አይነት ክስተት ግንኙነታቸውን እንደማይገልፅና እንደማያበላሽ አረጋግጠዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ቀደም ሲል ከጂቡቲ አቻቸው መሀመድ አሊ ዩሱፍ ጋር በሁለትዮሽና አካባቢ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም