የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ''ካለኝ ቀንሼ ለመከታዬ'' በሚል መሪ ሃሳብ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አደረጉ

97

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2014(ኢዜአ) የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ''ካለኝ ቀንሼ ለመከታዬ'' በሚል መሪ ሃሳብ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አደረጉ፡፡

የቀድሞ የጦር ጉዳተኞች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን ተሃድሶ እና የማህበራዊ ችግር ተጎጂዎች ልማት ማዕከላት ለመከላከያ ሰራዊት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

የቀድሞ የጦር ጉዳተኛ መቶ አለቃ ጥላየ ሽፈራው ማዕከላቸው ከጉዳተኞቹ የእንቁላል፣ ወተት እና የስጋ ወጫቸው ላይ ቀንሰው 289 ሺህ 741 ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ ህልውና እየተፋለመ ለሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ለመከላከያ ሰራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍና እገዛ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

በተመሳሳይ የአረጋዊያን ተሃድሶ ልማት ማዕከልና የማህበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማህበር በጋራ በመሆን 263 ሺህ 715 ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮም ለሰራዊቱ የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ተፈራ ሞላ፤ ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ የተቋሙ ሰራተኞች ደማቸውን መለገሳቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ቢሮውና በስሩ ያሉት ተቋማት የመከላከያ ሰራዊቱንና በጦርነት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያደርጉትን እገዛ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላት ጠብቆ ያቆያትን የመከላከያ ሰራዊት በመውጋት ክህደት የፈጸመውን ሃይል ለመደምሰስና ኢትዮጵያን ለማሻገር ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

ጦርነት ውድመትን የሚያመጣ ቢሆንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ሆኖ አገሩን እንዲጠብቅ ጦርነቱ እድል ፈጥሮልናል ብለዋል።

አገር አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን መከላከያው፣ ሚሊሻው፣ አርሶአደሩና ወጣቱ በግንባር በመሰለፍ እየተፋለሙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተደረገውን ድጋፍ የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስቴር ተወካይ ኮሎኔል ተስፋዬ መኮንን፤ ለሁሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን ከወራሪው ሃይል ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ ዜጎች የሚያደርጉት ድጋፍ ለሰራዊቱ ተጨማሪ የሞራል ስንቅ ሆኖታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም