ለአሸባሪዎች ድጋፍ በማድረግ ወንጀል በተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

49

ሐረር ፤ መስከረም 6/2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ለአሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ ድጋፍ በማድረግ ወንጀል በተጠረጠሩ15 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱን የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታወቀ።
የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዋና አቃቢ ህግ አቶ አዩብ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁትን ህውሃት እና ሸኔን በክልሉ የሚደግፉ ግለሰቦችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከህብረተሰቡ እና ጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በዚህም በክልሉ ለአሸባሪዎቹ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉ እና ለጥፋት የሚያነሳሱ ግለሰቦች እና ድርጅቶችን በመቆጣጠር የምርመራ እና ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ ክስ የመመስረት ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

አሁን ላይ ሽብርተኞችን በመደገፍ እና የሽብር ወንጀል በመፈጸም ወንጀል በተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች ላይ ክስ እንደተመሰረተ ነው  አቶ አዩብ  ያስታወቁት።

በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው ተጣርቶ ከወንጀሉ ነፃ ሆነው የተለቀቁ ግለሰቦች እንዳሉም አመላክተዋል።

እንዲሁም ሰባት ድርጅቶች ታሽገው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ባለንብረቶቹ ለጊዜው ቢሰወሩም 11 ተሽከርካሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሰዋል።

ሽብርተኞችን በመቆጣጠርና ወንጀልን በመከላከሉ ስራ ላይ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራልና ክልሉ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ሌሎችም የጸጥታ አካላት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ዋና አቃቢ ህጉ ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ሽብርተኞችን በማንኛውም መልኩ በመደገፍ የሀገርን ሰላም ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ድርጅቶችን ተከታትሎ ለህግ የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በክልሉ ወንጀልን የመከላከል ስራ ላይ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን ድጋፉን እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም