በአሸባሪው ህውሃት ንብረት የወደመባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ነው

70

ባህር ዳር መስከረም 5/2014 ( ኢዜአ) በደቡብ ጎንደር ዞን አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ሃብትና ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የህልውና ዘመቻው የሎጂስቲክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አወቀ ዘመነ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሃት በወራራ ይዟቸው በነበረው አራት ወረዳዎች ጉዳት አድርሷል።

ቡድኑ ያደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ፣ ከጎንደርና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች  የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን  የመጀመሪያ ዙር ጥናት ማካሄዱን ገልፀዋል።

 የሽብር ቡድኑ በገባባቸው ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች 108 ንፁሃን ዜጎች በግፍ መገደላቸውን ተናግረዋል።

"በርካታ ቁጥር ያላቸው መኖሪያ ቤቶች፣ የቤት እንስሳትና ንብረት መውደሙን  በጥናት ማረጋገጥ ተችሏል" ብለዋል።

አርሶ አደሩ እርስ በእርስ በመደጋገፍ የፈረሱ ቤቶችን መልሶ እየገነባ እንደሚገኝ ያመለከቱት ምክትል አስተዳዳሪው የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች መልሶ ለመገንባትና ለመጠገን 101 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በጥናት መመልከቱን አስታውቀዋል።

65 ሺህ ህዝብ መኖሪያ ቤቱ በመውደሙና ንብረቱ በመዘረፉ ለዕለት ምግብ እርዳታ መገደዳቸውን አስረድተዋል።

ምክትል አስተዳዳሪው አክለው ለተጎጅዎች ከህብረተሰቡ፣ ከአማራ ልማት ማህበር ፣ ከጥረት ኮርፖሬትና ከሌሎች  አካላት  1 ሺህ 300 ኩንታል የምግብ እህል ቀርቦ በቤተሰብ ደረጃ 25 ኪሎ ግራም እንዲሰራጭ ተደርጓል" ብለዋል።

ለህልውና ዘመቻው ከሁሉም የወረዳው አርሶ አደሮች የተሰበሰበ 4 ሺህ ኩንታል እህል ለተጎጅዎች  ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ በክልል ደረጃ የተዋቀረው ቡድን ከዞኑና ከወረዳ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት ጥናት መጀመሩን አስታውቀዋል።

በሽብር ቡድኑ የደረሱ ችግሮችን ለመፍታት ዞኑ 433 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ሃብት ለማሰባሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት ምክትል አስተዳዳሪው እስካሁን ከ270 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ መሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዞኑ የቅስና ሳህርና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መከተ አየነው በበኩላቸው "አሸባሪው ቡድን በሰው፣ በቤት እንስሳትና በሰብል ላይ ግፍና በደል አድርሷል" ብለዋል።

ወራሪዎቹ መኖሪያ ቤታቸውን በከባድ መሳሪያ ከማውደማቸው በፊት ሽሮና በርበሬ ሳይቀር እንደዘረፏቸው ገልጸው፤ ሴቶችንም አስገድደው መድፈራቸውን ተናግረዋል።

በፍልሰታ ፆም እንስሳትን በማረድ ሰርታችሁ ለእኛም ስጡን እናንተም መብላት አለባችሁ ብለው ያስገድዷቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ አልበላም ያለውን ደግሞ በመግደል ጭካኔ የተሞላበት ግፍ መፈጸማቸውን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከቤተሰብ ጋር ከነልጆቻቸው ተጠግተው እየኖሩ በመሆኑ የወደመ ቤታቸውን በአጭር ጊዜ ገንብተው ለመግባት ድጋፍ ጠይቀዋል።

የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ፣ ባለሀብቱ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም