ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ትኩረት የሰጠ መሪ እቅድ ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው

85

ድሬዳዋ መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) በኮቪድ 19 ክስተት የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ እንዲያገግም ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ትኩረት የሰጠ መሪ እቅድ ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዓለም ለ42ተኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ34ተኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን በድሬዳዋ እየተከበረ ነው፡፡

"ቱሪዝም ለሁለንተናዊ ዕድገት" በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ በሚገኘው የቱሪዝም ቀን  ዘርፉን ለማሳደግ በሚያስችልና ለቱሪስቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረጉ  የግንዛቤ ማስጨበጫ  ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር በወቅቱ እንዳሉት  በኮቪድ 19 ክስተት የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያገግም ለማስቻል መሪ እቅድ ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

መሪ እቅዱ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም ትልቅ ትኩረት የሰጠና ዘርፉ  ለሁለንተናዊ ልማት፣ ሰላምና ዕድገት እንዲውል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

እቅዱ ከፌደራል እስከ ክልል ባሉ አደረጃጀቶች ወጥና ተናባቢ ሥራ በመስራት ዘርፉን ዳግም ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ እንደሆነ አስታውቀዋል ።

ለእቅዱ ተግባራዊነት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ባለሃብቶች የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር አፈ-ጉባኤፈጡም ሙስጠፋ የቱሪዝም ዘርፍ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያነት  እንዲውል መትጋት እንደሚገባ አመልክተዋል ።

ድሬዳዋን  የቱሪዝም ኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ 1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ተመድቦ  የተለያዩ መሠረተ-ልማቶች እየተሟሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ አገግሞ በሀገር ሁለንተናዊ ልማት ላይ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙራድ በደዊ በበኩላቸው በሀገር አቀፍም   ሆነ በአስተዳደሩ ደረጃ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል ።

ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ትኩረት በመስጠትና የተቀናጀ ሥራ በመስራት ዘርፉ ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት እንዲውል እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 

በዘርፉ ውጤት ለማስመዝገብ በሆቴሎች ላይ የሚታዩ ችግሮች በመፍታት፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦችን ማራኪ በማድረግና  ማህበረሰባዊ የቱሪዝም ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

በድሬዳዋ እየተከበረ ባለው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በአል ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ወጣቶችና የሆቴል ባለቤቶች እየተሳተፉ ነው።

በዓሉ የቱሪዝም መስህቦችን በመጎብኘት ጭምር እየተከበረ መሆኑ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም