መጪዎቹን ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ለመታደም ወደ አገር ቤት የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንን ለመቀበል ዝግጅት ተጀምሯል

63
አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2010 ከመጪው ሣምንት ጀምሮ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን ለመታደም ወደ አገር ቤት የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያና ኤርትራን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማጠናከር ዓላማ ያለው አውደ-ርዕይና ሲምፖዚየም እንደሚዘጋጅም ገልጿል። ቡሄ፣ አሸንዳ፣ ኢድ አል-አድሃ (ዓረፋ)፣ ዘመን መለወጫ (ቅዱስ ዮሃንስ)፣ መስቀል እና ኢሬቻ ከተያዘው ሐምሌ አጋማሽ እስከ መጪው መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም በአገሪቱ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ናቸው። በእነዚህ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የአውደ ርዕዩና ሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች ናቸው። በተለይም በአሁኑ ወቅት በሰፈነው አንጻራዊ ሰላምና የመደመር ሂደት በዓላቱን ለመታደም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ይጠበቃል። ብሔራዊ ቲያትር፣ የባህል ማዕከልና ሌሎች ተቋማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ታዳሚዎቹን ማስተናገድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየሰሩ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና አስጎብኚ ድርጅቶችም እንግዶችን ለመቀበል እያሳዩ ያሉት መልካም ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል። ተቋማቱ ኢትዮጵያዊ ባህልን የተላበሰና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት በተለይ ኢትዮጵያዊያን ጎብኚዎች ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያስታውሱበት ድባብ መፍጠር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ጎብኚዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ወከባ እንዳይደርስባቸው፣ ስርቆትና ማጨበርበር እንዳይፈፀምባቸው ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ወይዘሮ ፎዚያ ጥሪ አቅርበዋል። ‘አንድ ሆነን አንድ‘በሚል መሪ ሃሳብ በሚከበሩት በዓላት ለሚታደሙ እንግዶች የሚደረገው አቀባበል የኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይነት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት፣ ባህላዊ እሴቶቻችንን ተጠቅመን ግጭቶችን የምናጠፋበትና ያለንን አንድነት የምናጠናክርበት ይሆናል" ብለዋል ሚኒስትሯ። ከኤርትራዊያን ጋር የተፈጠረውን አስደማሚ የሰላምና የአብሮነት ክስተት እንደ ዕድል በመጠቀምም ለዘመን መለወጫ በዓል አንድ የኤርትራ የባህል ቡድን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በቱሪዝም ዘርፍ ጠንካራ ትስስር በመፍጠር አገራቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ለመዘርጋት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ፣ በቱሪዝምና ባህል መስኮች ከሌሎች ጎረቤት አገራትም ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ትኩረት ሰጥታ የምትሰራ መሆኑን አክለዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ934 ሺህ በላይ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን ከዚህም ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም