የቡና አምራች ገበሬዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የወጪ ንግድን ያሳድጋል የተባለ ስምምነት ተፈረመ

70

መስከረም 5/2014 (ኢዜአ) የቡና አምራች ገበሬዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የወጪ ንግድን ያሳድጋል የተባለ ስምምነት ተፈረመ።

የተደረሰው ስምምነት ብሌስ ኮፊ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ ከተባለ ድርጅት፣ ከፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲና ከሚመለከተታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መሆኑ ታውቋል።

በስምምነቱ መሰረት በኢትዮጵያ የሚገኙ የቡና አምራች ገበሬዎች በህብረት ስራ ማህበራትና በዩኔየን በኩል ከድርጅቱ ጋር የሚሰሩ ይሆናል።

የንግድና ኢዱስትሪ ሚኒስር ዴታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፤ የተደረገው ስምምነት በቡና ምርት ላይ እሴት በመጨመር በተለይም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች በማቅረብ ገቢን ማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመጀመሪያ ሙከራ ቡናን እሴት ጨምሮ ወደ አሜሪካ ግዛቶች ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪ ላንድና  ቨርጂኒያ የሚላክ ይሆናል።

ኢትዮጵያ በቡና ንግድ ያላት ተሳትፎ ስኬታማ እንዲሆን ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አምባሳደር ምስጋኑ አረጋግጠዋል።

የቤኔፊት ፎር አፍሪካ ኮኦፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ እና  ብሌስ ኮፊ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ መስራች አቶ ጥበቡ አሰፋ፣ የኢትዮጵያ የቡና ምርት በዓለም ገበያ ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኦስማን ሱሩር፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ99 ሺህ በላይ  የህብረት ስራ ማህበራት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የቡና አምራች ገበሬዎችም የህብረት ስራ ማህበራት አባል በመሆናቸው በአዲሱ የስረራ ጥምረት ተጠቃሚ የሆናሉ ብለዋል።

ቤኔፊት ፎር አፍሪካ ኮኦፖሬሽን በቡና ምርት ለይ የጀመረውን የጋራ ተጠቃሚነት ጥምረት በሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ ለማስፋት እቅድ እንዳለው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም