በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ እንደሚሰሩ የአፋር ህዝባዊ ፓርቲና የአፋር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቁ

87
አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2010 በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ እና ከመንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው የአፋር ህዝባዊ ፓርቲና የአፋር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቁ። ከኢትዮጵያ ውጭ መቀመጫቸውን ያደረጉት የፓርቲውና የድርጅቱ ሊቀ መናብርት ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል። የአፋር ህዝባዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ እና የአፋር የሰብዓ መብት ተሟጋች ድርጅት ሊቀ መንበር አቶ ገኃስ አህመድ ከመንግስት ጋር በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። ዶክተር ኮንቴ ሙሳ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ ለመደገፍና በአፋር ክልል የሚታዩትን ችግሮች ለማስወገድ በትብብርና በጋራ ለመሥራት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ከ14 ዓመት በፊት በአፋር ክልል የነበረውን የአስተዳደር በደል፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትህ መጓደል፣ አሳታፊ ያልሆኑ የልማት ሥራዎችን በመቃወም ፓርቲው እንደተቋቋመ አስታውሰዋል። በውጭ አገር ቆይታቸው ያገኙትን ልምድና እውቀት በመጠቀም እንዲሁም በጥናት ላይ የተመሠረተና የክልሉን ህዝብ ያሳተፈ ሥራ በአፋር ክልል ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የአፋር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሊቀ መንበር አቶ ገኃስ አህመድ በበኩላቸው ባለፉት 12 ዓመታት የህዝብን ችግር፣ ሰቆቃ፣ ከመሬት መፈናቀል፣ እስራትና የፍትህ መጓደልን በተመለከተ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች በኩል ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የመጣውን ለውጥ ለመደገፍና ለማስቀጠል ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ገልጸዋል። በተለይ ከወጣቶች፣ ከሴቶችንና ከተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር ለአፋር ክልልና ለአገሪቱ የሚጠቅም ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በስደት ይኖሩ የነበሩት የአፋር መንፈሳዊ አባትና ባህላዊ መሪ ሱልጣን ሐንፍሬ አሊሚራህ፣ የአፋር ህዝባዊ ፓርቲ፣ የአፋር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅትና የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር በውጭ አገር ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም