በአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ተሸፍኗል

162

አዲስ አበባ መስከረም 5/2014 (ኢዜአ)በአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል መሸፈኑን የከተማ አስተዳደሩ የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽነር መኮንን ሌንጂሶ፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ በ2013/14 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ እየተሰሩ ያሉ የግብርና ሥራዎችን ከክፍለ ከተማው አመራሮች ጋር በጋራ ጎብኝቷል።

መንግስት አርሶ አደሩን መልሶ በማቋቋም እንዲሁም የሥራ እድል በመፍጠር በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲሁም ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2013/14 የመኸር እርሻ ወቅት በከተማዋ የሚገኙ አርሶ አደሮች በተሻለ የአስተራረስ እና የአዘራር ዘዴ ጤፍ እና ስንዴ መዝራት መቻላቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል ኮሚሽነሩ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መኮንን አምባዬ በበኩላቸው፤ በክፍለ ከተማው "ምግባችን ከደጃችን ምርታችን ከአካባቢያችን" በሚል መርህ 400 አርሶ አደሮች በመኸር እርሻ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮቹ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት እንዲያርሱ መደረጉንም ገልጸው ከ930 ኩንታል በላይ ማዳበሪያና የጤፍ፣ የስንዴ፣ የሽምብራ እንዲሁም የምስር ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች መቅረቡን ጠቁመዋል።

በዚህም ከ2 ሺህ 700 ቶን በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ በከተማ ግብርና ተሰማርተው የሚገኙት አርብቶ አደር አዜብ ኤፍሬም በ30 ኪሎ ጤፍ ምርት የጀመሩት ሥራ አሁን ላይ ከ6 እስከ 7 ሚሊዮን ብር በላይ  ካፒታል እንዳላቸው ገልጸዋል።

በሥራቸው ለ20 ሠራተኞችም የሥራ እድል የፈጠሩ ሲሆን ከከብት እርባታ በተጨማሪ በንብ ማነብ እንዲሁም የባልትና ውጤቶችን በማዘጋጀት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር እሸቴ ገመቹ፤ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ በመቅረቡ ያለምንም እንቅፋት ሥራቸውን ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ አርሶ አደሮቹ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም