በህገ ወጥ መንገድ ሲሰሩ በተገኙ 276 ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወሰደ

73

ጎባ መስከረም 5/2014 (ኢዜአ) የምርት ዋጋን በማናር ጨምሮ በህገ ወጥ መንገድ ሲሰሩ በተገኙ 276 ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን የባሌ ዞን ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

እርምጃው የተወሰደው በዞኑ አስራ ሁለት ወረዳዎች ውስጥ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የምዝገባና ፍቃድ አሰጣጥ አስተባባሪ አቶ አብዱልሀኪም መህሙድ ለኢዜአ እንደገለጹት ህጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ነጋዴዎች ያልተገባ ዋጋ የጨመሩ፣ ደረሰኝ የማይቆርጡ፣ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ምርት ይዘው የተገኙ፣ ያለ ንግድ ፍቃድ ሲሰሩ የተገኙ ናቸው።

በዚህም የ138 ነጋዴዎች የንግድ ተቋማት ሲታሸጉ፤ 132ቱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ከድርጊታቸው መማር ያልቻሉ ሌሎች  ነጋዴዎች ደግሞ ጉዳያቸው ለህግ ቀርቦ እየታየ መሆኑን ነው ያወሱት።

"ችግሮችን በጋራ ተቋቁመን የምናልፍበት እንጂ ትርፍ የምናካብትበት ጊዜ አይደለም" ያሉት አስተባባሪው፤ በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ አብዱልሀኪም ገለጻ፤  የገበያ ማረጋጋት ግብረ ኃይሉ እያደረገ በሚገኘው ዕለታዊ ክትትል ከዚህ በፊት ዋጋን በመጨመር ከፍተኛ ቅሬታ በሚሰማባቸው ወረዳዎች ላይ ለውጥ  ማምጣት ተችሏል።

በዞኑ ህጋዊ የንግድ ስርዓትን ያልተከተሉ ግብይቶችን የሚያካሄዱ ነጋዴዎችን በማስተማርና ህግን አልፈው በሚገኙ ላይ የህግ እርምት እየተወሰደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የግብረ ኃይሉ አባል የዞኑ ዐቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልዋሂድ አብዱረህማን ናቸው፡፡

ከጎባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አበባ ገመቹ በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት በስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የሚያደርገው ክትትል ወጥነት ሊኖረው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ወቅቱን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በህገ ወጥ ተግባር በመሰማራት በህዝብ ላይ ተጨማሪ በደል እያደረሱ በሚገኙ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሙንተሃ አብደላ ናቸው፡፡

በባሌ ዞን ከ11 ሺህ የሚበልጡ ህጋዊ ነጋዴዎች በተለያዩ ደረጃ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ከዞኑ ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም