አሸባሪው ህውሃት የከፈተው የውክልና ጦርነት የመተሳሰብ እሴታችን ይበልጥ እንዲጎለብት አስችሏል

194

ባህርዳር መስከረም 5/2013 "አሸባሪው ህውሃት የከፈተው የውክልና ጦርነት የአንድነትና የመተሳሰብ እሴታችን ይበልጥ እንዲጎለብት አስችሏል" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ  አስተዳደር ህወሃት በከፈተው  ጦርነት ጉዳት ለደረሰበት የአማራ  ክልል  የ385 ሚሊየን ብር ድጋፍ ዛሬ አበርክቷል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ  በወቅቱ እንዳሉት  መንግስት ህወሃት  ሀገር  ከማፍረስ  ሴራ እንዲመለስና አውዳሚ ጦርነት  እንዳይከሰት በማሰብ  ሸምጋዮችን  በመላክ ጭምር እራሱን ዝቅ በማድረግ ብዙ ጥረት አድርጓል ።

"ይሁን እንጂ አሸባሪው ቡድን እብሪቱ ሞልቶ በመፍሰሱ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ  በመሆን የውክልና ጦርነት በመክፈት በንጹሃን ዜጎች ላይ ግፍና በደል እየፈጸመ  ይገኛል" ብለዋል ።

ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለመበታተን ወደ  ኋላ እንደማይል  በግልጽና በአደባባይ  መናገሩን  አመልክተዋል።

ህወሃት ከመከላከያ ሰራዊት የራሱን ሃይል  በማስወጣት በሌሎች የሰራዊት  አባላት ላይ  ብሄርና ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ  በመፈጸም ታሪክ የማይረሳ  ጠባሳ  ማሳረፉን ተናግረዋል።

"በአሸባሪው እኩይ ድርጊት ተገደን የገባንበት ጦርነት  ፍትሃዊና ኢትዮጵያን  የማዳን  ግዴታ  መሆኑን አውቀን ሁላችንም በመረባረብ ጦርነቱን  ባጭር ጊዜ በማጠናቀቅ  ወደ  ልማታችን መዞር ይገባናል" ብለዋል።

"ጦርነቱ የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር፣ የህዝባችንን ትስስርና ትብብር በማጎልበት መልካም እድል ይዞ መጥቷል" ያሉት ወይዘሮ አዳነች የተረሳውን የመተሳሰብና በጋራ  የመቆም አሴት አዳብሮታል" ብለዋል።

ከአሁን በኋላ ማንኛውም የውጭም ሆነ የውስጥ ሃይል በየትኛውም ቦታ ኢትዮጵያን መድፈር እንደማይችል በተግባር የተረጋገጠበት ሁኔታ መፈጠሩን አስገንዝበዋል።

"አሁን ላይ በጦርነቱ የበላይነት ማግኘታችን በቀጣይ በአገራችን ልማትና እድገት ለምንሰራው ስራ የሚያበረታታን ነው" ያሉት ወይዘሮ አዳነች "በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎችን መደገፍ ይገባናል" ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ነጋዴዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር በጦርነቱ ለተጎዳው የአማራ ክልል ከ385 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ይዘው መቅረባቸውን ወይዘሮ አዳነች አስታውቀዋል ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው "ጦርነቱ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያለመ ቢሆንም በታሪክ አጋጣሚ አዋሳኝ በመሆናችን ህዝባችንን ለማዋረድና  አንገት ለማስደፋት ወረራ ተፈጽሞብናል" ብለዋል።

ህወሀት በደቡብና በሰሜን ወሎ፣ በሰሜንና በደቡብ ጎንደር እንዲሁም በዋግ ኽምራ አካባቢዎች ወረራ በመፈጸም ንጹሃንን በመግደል፣ ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ግፍ መፈጸሙን አስረድተዋል።

አሸባሪው ቡድን በፈጸመው ወረራ ከ550 ሺህ በላይ ህዝብ ቀየውን ለቆ፣ ሀብትና ንብረቱን ትቶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መፈናቀሉን አመልክተዋል።

ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከ4 ሚሊየን በላይ ህዝብ ረሀብ ተጋርጦበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አቶ አገኘሁ አክለው መከላከያ ሰራዊታችንና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ወረራውን ለመቀልበስ ልብስ ሳይቀይሩ ለ10 ወራት በግንባር እየተፋለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወራሪውን ሃይል በመጣበት አግባብ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ በተላላኪነት ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችል ለማሳየት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

"ምንም እንኳ አሸባሪው ቡድን የክልሉን ህዝብ ተስፋ ለማስቆረጥ ወረራ ቢፈጽምም ወራሪው ሀይል ከክልላችን ሳይወጣ በመቅበር ጦርነቱን በድል እንወጣለን " ብለዋል።

"ለአዲስ አበባ መስተዳድር ማህበረሰብ የምናረጋግጠው ሞተንና መስዋዕትነት ከፍለን ድሉን ባጭር ጊዜ የምናስመዘግብ መሆኑን ነው" ሲሉም በጽናት ተናግረዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ወልድያና ቆቦ የእርዳታ እህል ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አገኘሁ ሌሎቹም በእለት ምግብና በመልሶ መቋቋም እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም