በዘርፉ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተገልጋዮች የመልካም አስተዳደር ችግር መኖራቸውን ያምናሉ-ጥናት

106
አዲስ አበባ ነሃሴ 8/12/2010 በከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍ ከ 60 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተገልጋዮች የመልካም አስተዳደር ችግር መኖራቸውን እንደሚያምኑ ጥናት አመለከተ። የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን አክስዮን ማህበር ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያካሄደው የህዝብ አስተያየት የዳሰሳ ጥናት ዛሬ ይፋ ሆኗል። በጥናቱ ግኝት ላይ ከ9ኙ ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ባለሙያዎች፣ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ጥናቱ ''የመሬት ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ላይ የመልካም አስተዳደር ያለበት ሁኔታ'' በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ከተመረጡ 12 ከተሞች ናሙና ተወስዷል። ለዚሁ ጥናት አራት ተቋማት የተለዩ ሲሆን መሬት ልማትና ከተማ ማደስ፣ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ፣ የይዞታ አስተዳደርና ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ናቸው። ዜጎች ስለ ስምምነት ሰነድ/የዜጎች ቻርተር/ መኖር ምን ያህል ያውቃሉ?፣ በልማት ሥራዎች ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ያለበት ደረጃ፣ በመስኩ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበት ደረጃና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተገልጋዮች ምን ያህል ይረካሉ? የሚሉ ጉዳዮች ተዳስሰዋል። ጥናቱን ያቀረቡት በማህበሩ ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ አስቻለው ወርቁ እንደገለጹት፤ ለጥናቱ ወካይ የሚሆን ናሙና የተወሰደው ከመቀሌ፣ አክሱም፣ ባህር ዳር፣ ደሴ፣ አዳማ፣ አዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ አሶሳና ሰመራ ናቸው። እድሜያቸው ከ 18 ዓመት በላይ ለሆኑ 4ሺ 362 ተገልጋዮች ጥያቄው የቀረበ ሲሆን ከነዚህም 4ሺ 126 ሰዎች ጥያቄውን ሞልተው መመለሳቸው ተገልጿል። በዚህም መሰረት በአማካይ 60 በመቶ የሚሆኑ ተገልጋዮች የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን በሰጡት ምላሽ አሳውቀዋል። ከመላሾቹም አድሎኣዊ አሰራር፣ የግልጽነት ጉድለት፣ ተገልጋይን ማበላለጥ እንዲሁም ያልተገባ ጥቅም ፈላጊ አመራርና ፈጻሚዎች አሉ ብለው እንደሚያምኑም በጥናቱ ተረጋግጧል ነው ያሉት ተመራማሪው። ከዚህ ባለፈም ከ51 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተገልጋዮች ደግሞ የሚሰጠው አገልግሎት አርኪ አለመሆኑ በጥናቱ ተገኝቷል ብለዋል። እንደ አቶ አስቻለው ገለጻ በዘርፉ ስር ያሉ ተቋማት ውስጥ የቅንጅት ማነስ፣ ተገልጋዮች በምን ያህል ግዜ ውስጥ መስተናገድ እንዳለባቸው አለማወቅን የመሳሰሉ ጉዳዮችም በጥናቱ መለየታቸውን አብራርተዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከአዲስ አበባ ምክር ቤት ሕግና ፍትህ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመጡት አቶ ዋለልኝ መኩሪያ እንደሚናገሩት የህዝቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የተጠያቂነት አሰራር በተጠናከረ መልኩ ገቢራዊ ማድረግ ያሻል። ከድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የመጡት ኮማንደር ቢንያም ፍቅሬ በበኩላቸው የዳሰሳ ጥናት ውጤቱን መሰረት በማድረግ በፍጥነት ጥልቅ ጥናት  ማካሄድ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ አቶ ዣንጥራር አባይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ጥናቱ መልካም አስተዳደር ላይ ተገልጋዩ ምን አይነት አተያይ አለው? የሚለውን ለማወቅ የተደረገ ጥናት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ሚኒስቴሩ ግኝቱን በመንተራስ ጠለቅ ያሉ ጥናቶችን በማድረግ የመፍትሄ እርምጃዎችን ይወስዳል ብለዋል። የዜጎች ቻርተር/ስምምነት ሰነድ/ ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር በመገናኛ ብዙሃን፣ በማህበረሰብ ሬዲዮና በበራሪ ወረቀቶች በመጠቀም በቀጣይ ርብርብ እንደሚደረግም አመልክተዋል። በተለይ ''የአገልግሎት እርካታ ላይ ለምን ክፍተት መጣ የሚለው ተከታታይነት ያለው ጥናት ያስፈልጋል'' ያሉት ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ የየክልል ፕሬዝዳንቶችና የሚመለከታቸው አካላት እንዲሰሩበት አቅጣጫ ይቀመጣል ብለዋል። ከአገልግሎት ቅልጥፍና ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን በተለይ ዘመናዊ አሰራሮችን በመከተል ለመፍታት ይሰራል ሲሉም አብራርተዋል። ውይይቱ ነገም የሚቀጥል ሲሆን ዛሬ ይፋ ያልተደረጉ ሁለት የዳሰሳ ጥናት ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ይጠበቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም