በዞኑ በ114 ሚሊዮን ብር ግንባታቸው የተጠናቀቀ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል

157

መቱ መስከረም 4/2014 (ኢዜአ) በኢሉ አባቦራ ዞን በ114 ሚሊዮን ብር ግንባታቸው የተጠናቀቀ የኢፋ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ለመቀበል ምዘገባ መጀመራቸውን የዞኑ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የኢሉባቦር ዞን ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ነገሱ ለኢዜአ እንደገለፁት ትምህርት ቤቶቹ በአልጌ ሳቺና በያዮ ወረዳዎች የተገነቡ ናቸው፡፡


ትምህርት ቤቶቹ አስፈላጊው የትምህርት ግብዓቶች ተሟልቶላቸው ተማሪዎችን ለመቀበል ምዝገባ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው 2014 ትምህርት ዘመን ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ 1ሺህ 154 ተማሪዎችን እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።

የያዮ ወረዳ ዊጣቴ ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ ቶፊቅ አብደላ ከዚህ በፊት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ለመከታተል ብዙ ርቀት ይጓዝ እንደነበር ተናግሯል።

ዘንድሮ በአቅራቢያቸው የተገነባው ትምህርት ቤት ስራ ለመጀመር ተማሪዎችን በመመዝገብ ላይ በመሆኑና የእድሉ ተጠቃሚ በመሆኑ መደሰቱን ገልጻል።

“በአካባቢያችን የተገነባው ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀና አስፈላጊ ግብዓቶችም የተሟሉለት ስለሆነ ጥራት ያለው ትምህርት እናገኝበታለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ያለው ደግሞ በአልጌ ሳቺ ወረዳ የሳቺ ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ ተመስን ብሩ ነው።